(ታሕሳስ 24/2018 ዓ.ም) በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ገልጸዋል።
በእንስሳት ሃብት ልማት የሚስተዋሉ ችግሮችን እየፈቱ መኾናቸውንም ጠቁመዋል።
የቦታ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት በኩታገጠም ደረጃ በማሰባሰብ ሼዶችን መገንባት ላይ ትኩረት ተደርጓል ነው ያሉት።
ለአብነትም በዶሮ ርባታ እና በእንቁላል ምርት ከ49 በላይ ሼዶች ያሉበት የዶሮ ኩታገጠም መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።
በዚህም ሞዴል የዶሮ ኩታገጠም በማዘጋጀት እና አርቢዎችን በማሠባሠብ ዘርፉን ለማዘመን እየተሠራ ነው ብለዋል።
ለወተት ሃብት ልማትም ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራቱ በከተማዋ ምርቱ እየጨመረ መጥቷል ነው ያሉት።
በከተማዋ 27 የሚኾኑ የመሸጫ ሱቆች ተከፍተው ወደ ሥራ በማሥገባት የገበያ ትስስር ችግርን እየፈታን ነው ብለዋል።
የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች እንዲኖሩ ለማድረግም ጥረት እየተደረገ መኾኑን አንስተዋል።
በከተማዋ በሥጋ ምርት የቆየ ልምድ እና አቅም መኖሩንም አንስተዋል። በዘመናዊ መንገድ በማስፋት የራሱ መለያ እንዲኖረው ለማድረግም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።
በዓሣ ሀብት ልማትም ከጣና ሐይቅ በተጨማሪ በዘመናዊ የኩሬ ኩታገጠም በማልማት የዓሣ ምርትን ለማሣደግ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ባሕር ዳርን በእንስሳት ሀብት ልማቷ የተሞክሮ ማዕከል እንድትኾን ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ይህንን ለማሳካትም በወተት ላም ርባታ፣ በከብት ማድለብ፣ በዶሮ ርባታ፣ በዓሣ እና በማር ልማት በዘመናዊ መንገድ ለመሥራት 32 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መገባቱን አመላክተዋል።

