የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጥርን በተለያዩ ኩነቶች ለማክበር ሰፊ ዝግጅት አድርጓል።
(ታሕሳስ 23/2018 ዓ.ም) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር “ጥርን በባሕር ዳር እስከ ጥር 30/2018 ዓ.ም ድረስ በልዩ ልዩ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ኩነቶች ለማክበር የተሟላ ዝግጅት መደረጉን ገልጿል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የ”ጥርን በባሕርዳር” ዝግጅት አስመልክተው በጽሕፈት ቤታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የዘንድሮው የጥርን በባሕርዳር ክብረ በዓል የከተማዋን የባሕል፣ የሃምነት፣ የአንድነት እና የቱሪዝም መዳረሻነት በሚያጎላ መልኩ ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሠራቱን ጠቁመዋል።
በበዓሉም የገና ጨዋታ፣ ከተማዋን የማጽዳት እና የማስዋብ ሥራ፣ የመጽሐፍ ዐውደ ርዕይ፣ የብስክሌት ሽርሽር፣ የከተራ በዓል፣ የታንኳ ቀዘፋ፣ የፊልም እና የኪነ ጥበብ ምሽት፣ የሥነ ምግብ ፌስቲቫል እና በሌሎች ዝግጅቶች በድምቀት እንደሚከበሩ ተናግረዋል።
“በዋናነት ጥር 18/2018 ዓ.ም የሚከበረው የሰባር ጊዮርጊስ በዓልን በድምቀት በማክበር ለዓለም የምናስተዋውቅበት ይኾናል” ነው ያሉት።
ይህ ዝግጅት የከተማዋን ባሕላዊ እሴቶች ለማሳደግ፣ የሕዝብ መተባበር፣ አንድነትን ለማጠናከር እና ቱሪዝምን ለማበረታታት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
በዓሉን ለማክበር ከተማዋን የማጽዳት እና የማስዋብ ሥራዎች መሠራታቸውንም ተናግረዋል።
በተጨማሪም የበዓሉ ዝግጅቶች በሰላም እና በደኅንነት እንዲከናወኑ ከጸጥታ አካላት፣ ከኅብረተሰቡ እና ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል።
እንግዶችን ለመቀበልም ሆቴሎች፣ ሎጅዎች እና አስጎብኝ ድርጅቶችም ተዘጋጅተው እየተጠባበቁ መኾኑን ተናግረዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የባሕር ዳር ነዋሪዎች የአካባቢ እና የውጭ ጎብኝዎች የጥር በዓልን በሰላም እንዲያከብሩ አስፈላጊውን እገዛ ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

