በምዕራብ ጎጃም ዞን በቋሪት ወረዳና አካባቢው ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ገቡ።
በወረዳው ትጥቅ ይዘው ጫካ የነበሩ ታጣቂዎች መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው መግባታቸውን የቋሪት ወረዳ አስተዳድር ገለጸ።
በወረዳው ጣሊያን፣ ወይበይኝ፣ ብር አዳማና አጎራባች ቀጠናዎች ላይ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች መገዳደል ለቋሪትና አካባቢው ህዝብ ያስገኘው ትርፍ እንደሌለ በመረዳት መንግስት ያስቀመጠውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው መግባታቸው ተገልጿል።
የቋሪት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መኳንት ወርቅነህ እንደገለጹት ታጣቂዎቹ በተሳሳተ መንገድ ተደናግረው ወደ ጫካ ገብተው የነበረ ቢሆንም ዛሬ ላይ ቆም ብለው አስበው የሰላምን መንገድ መከተላቸው የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።
ሌሎች ታጥቀው በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላትም ወደ ሰላም መጠው መደበኛ ህይወታቸውን እንዲቀጥሉ አቶ መኳንት ጥሪ አቅርበዋል።
ለሰላም እጅ የሰጡ ታጣቂዎች በበኩላቸው ባልተገባ መንገድ ወደ ጫካ ገብተን የራሳችንን ማህበረሰብ የከፋ ችግር ላይ በመጣላችን ተጸጽተናል ሲሉ ገልጸዋል።
በጦርነት የሚፈታ ችግር የለም ያሉት ወጣቶቹ አሁንም ተደናግረው ጫካ ያሉ ጓደኞቻችን ከዚህ በኃላ መገዳደል በቃን ብለው የሰላምን መንገድ ተከትለው እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።

