ከተቀጣሪነት ይልቅ ሥራ ፈጣሪነትን የመረጡ ብርቱ ወጣቶች!

(ታሕሳስ 24/2018 ዓ.ም) ወጣት ሙሉ ብርሌው በባሕር ዳር ከተማ አጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ በዶሮ እርባታ ዘርፍ ተሰማርቶ እየሠራ አግኝተነዋል።

ወጣቱ ለአሚኮ እንደገለጸው በመጀመሪያ ዲግሪ ከተመረቀ በኋላ ተቀጣሪ ኾኖ ከመሥራት ይልቅ ሥራ ፈጣሪ ኾኖ መሥራትን መርጧል።

በመንግሥት በኩል ባገኘው የመሥሪያ ቦታ እና የሙያዊ ድጋፍ ሥራውን በ2004 ዓ.ም በ2 ሺህ ብር ካፒታል መጀመሩን ነግሮናል።

አሁን ላይ 1 ሺህ 100 የእንቁላል ዶሮዎችን እያረባ በአማካኝ በቀን እስከ 900 እንቁላል ለገበያ እያቀረበ እንደሚገኝ ነው የገለጸልን።

በአሁኑ ወቅት ካፒታሉን ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ማድረስ እንደቻለ ገልጿል።

በቀጣይም በስፋት በመሥራት በቀን 10 ሺህ እንቁላል ለማምረት እንዳቀደ ነው የተናገረው።

ሌላኛው በዶሮ እርባታ ዘርፍ ተሠማርቶ ያገኘነው ወጣት መሳይ ታምራት ከጓደኞቹ ጋር ማኅበር መሥርተው በ2017 ዓ.ም ሥራውን መጀመራቸውን ተናግሯል።

ወጣቱ እንደገለጸው ከ2 ሺህ በላይ የእንቁላል ዶሮዎችን እያረቡ በቀን ከ1 ሺህ 600 በላይ እንቁላል ያገኛሉ። ከ7 ሺህ በላይ ጫጩቶች እንዳሏቸውም ገልጿል።

በመንግሥት በኩል የመሥሪያ ቦታ ድጋፍ፣ ሙያዊ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገላቸው ስለመኾኑም ጠቁሟል።

በአሁኑ ወቅት የማኅበሩ ካፒታል ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ብር መድረሳቸውን ነው የገለጸው።

ወጣቶች ተደራጅተው ሥራ ሳይንቁ ቢሠሩ በዘርፉ ውጤታማ መኾን እንደሚችሉ ነው አስተያየቱን የሰጠው።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ውለታው አዳነ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርን ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

የእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ዘርፍን ለማዘመን ከተማ አሥተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን አንስተዋል። ለአብነትም ለዶሮ እርባታ የሚኾን 3 ነጥብ 2 ሄክታር መሬት ተለይቶ ሼዶችን በመገንባት በስፋት ለማልማት እየተሠራ መኾኑን አስታውቀዋል።

የተሻሻሉ የዶሮ ዝርያዎችን ማከፋፈል፣ የአንድ ቀን ጫጩቶችን ለአርቢዎች ማሠራጨት እና ባለሙያዎችን በመመደብ የተጠናከረ የክትትል እና ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።

በከተማ አሥተዳደሩ 125 ኢንተርፕራይዞች እና 3 ሺህ 750 የግል አርቢዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top