በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ለተከታታይ ቀናት ስልጠናቸውን ሲከታተሉ የነበሩ የሰላም አስከባሪ አባላት ተመረቁ።

የኮምቦልቻከተማ አስተዳደር ሚሊሻ ጽ/ቤት ለተከታታይ ቀናት በተግባር እና በንድፈ ሃሳብ ሲያስጥናቸው የነበሩ የሰላም አስከባሪ አባላት በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙሀመድአሚን የሱፍ በምረቃ መርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ሰላም አስከባሪ ኃይላችን በወታደራዊ ስነ- ምግባር ታንጾ የህዝብ አለኝታነቱን እንዲያረጋግጥ ስልጠናው አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በተሰጠው ስልጠና አቅማችሁን በማጎልበት ሀገርንና ህዝብን በማስቀደም ከውስጥ ባንዳም ሆነ ከውጭ ባዳ የሚነዙ ፕሮፖጋንዳ ሳይበግራችሁ የከተማችንንም ሆነ የክልላችንን ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የድርሻችሁን እንድትወጡ ብለዋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በየዘመኑ ያጋጠሟትን ችግሮች በጀግኖች ልጆቿ እየተወጣች መምጣቷን ያነሱት ከንቲባው አሁንም በጀግኖች ልጆቿ ሉአላዊነቷን አስጠብቃ ትቀጥላለች ብለዋል።

የታሪካዊ ጠላቶቻችንን ተልዕኮ በማንገብ ቀጣናውን ለማተራመስ የሚጥሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም ጠይቀዋል።

ሰላም አስከባሪ ሠራዊታችን ለተከታታይ ቀናት በወሰደው ወታደራዊ ስልጠና አቅሙን በማሳደግ እና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የህግ የበላይነት እንዲያስከብር አሳስበዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ሰይድ ዓሊ በበኩላቸው እንደ ከተማችን የሰላም አስከባሪ ሰራዊቱን አቅም ለመገንባት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ በመሆኑ በውጤት የታጀበ ነው ብለዋል።

የሰላም አስከባሪ ሰራዊቱ የከተማውን ብሎም የክልሉን ሰላም ለመንሳት የሚንቀሳቀሰውን ጽንፈኛ ቡድን ለህግ ተገዠ ለማድረግ ከሚንጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ ሚሊሻ ጽ/ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ጌታዎይ ዘገየ እንደተናገሩት የሰላም አስከባሪ ኃይላችን የከተማዋን ዘላቂ ሰላም ከማረጋገጥ ባለፈ ሀገራችንን ከውጭ ጠላት ከውስጥ ባንዳ ለመጠበቅ ከምንግዜውም በላይ የስነ ልቦና ወታደራዊ አቅሙ አድጓል ብለዋል።

ሰልጠኞቹ የአካል ብቃት፣ የተኩስ እና ልዩ ልዩ ወታደራዊ ስልጠናዎች ያጠናቀቁ መሆናቸውን ኮሎኔል ጌታዎይ ዘገየ ገልጸዋል።

ተመራቂ የሰላም አስከባሪ አባላት በበኩላቸው በስልጠና ቆይታቸው በሙያው በቂ ወታደራዊ ዕውቀት እና በተግባር የታገዘ ወታደራዊ ልምድ ማግኘታቸውንና ለተልዕኮም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አማካሪ ኮሎኔል ባምላኩ አባይ ፣ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅርጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ አቢ፣ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ወንዶሰን ልሳነወርቅን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት መኮነኖች እና የፌደራል ፖሊስ አባላት መገኘታቸውን ከኮምቦልቻ ከተማ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top