(ታሕሳስ 15/2018 ዓ.ም) ወጣት መላኩ ታደሰ በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በዶሮ እርባታ ሥራ ተሰማርቶ አግኝተነዋል።
ወጣቱ እንደገለጸው ለ11 ዓመታት ያህል በመንግሥት ሥራ ላይ ቆይቷል። የሁለተኛ ዲግሪም ይዟል።
ነገር ግን በመንግሥት ሥራው የሚያገኘው ገቢ ሕይዎቱን በሚፈልገው መንገድ መለውጥ እንዳልቻለ ይገነዘባል።
ሠርቶ የመለወጥ መሻትን እውን ለማድረግ በግሉ ወደ ዶሮ እርባታ መሠማራቱንም ይገልጻል።
በሂደትም ከጓደኞቹ ጋር ማኀበር መሥርተው ከባንክ 40 ሺህ ብር ብድር በማግኘት የዶሮ እርባታ ሥራን በጋራ መጀመራቸውን ነግሮናል።
በአሁኑ ወቅት ሦሥት አይነት ዝርያ ያላቸውን ዶሮዎች በማርባት ተጠቃሚ መኾናቸውንም ገልጿል።
6ሺህ የእንቁላል ጣይ ዶሮዎች እንዳሏቸውም ነው የተናገረው። በቀን በአማካይ ከ5ሺህ በላይ እንቁላል እናገኛለን ነው ያለው።
ማኀበሩ በወር እስከ 500 ሺህ ብር ድረስ ገቢ እንደሚያገኝም ተናግሯል። እስከ መተማ እና ሱዳን ድረስ የገበያ ትስስር እንዳላቸውም ጠቁሟል።
በዚህም የመለወጥ ፍላጎትን እውን ማድረግ እንደቻሉ ነው ወጣቱ የሚገልጸው።
ሌላኛዋ በዶሮ እርባታ ዘርፍ ተሰማርተው ያገኘናቸው ጽላተማርያም ተመስገን በ50 ዶሮዎች በመኖሪያ ቤታቸው መጀመራቸውን ይገልጻሉ።
በአሁኑ ወቅት መንግሥት ባመቻቸላቸው ሦሥት ክላስተሮች ከ60 ሺህ በላይ ዶሮዎች እንዳሏቸው ገልጸዋል።
በቀን በአማካይ ከ40 ሺህ በላይ እንቁላል ለገበያ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።
በዚህም እስከ አዲስ አበባ፣ መቀሌ እና ሱዳን ድረስ የገበያ ትስስር እንዳላቸው ነው የተናገሩት። ለ137 ዜጎችም የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
ከቤተሰብ ጀምሮ ማኀበረሰቡ ያለው ዝቅተኛ አመለካከት፣ የመኖ አቅርቦት እና የአንድ ቀን ጫጩት እጥረቶች ፈታኝ መኾናቸውንም ጠቁመዋል።
ይህንን በማለፍ ለዚህ ደረጃ በመብቃታቸው ደስተኛ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ካጋጠማቸው ችግር በመነሳትም በቀጣይ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፍብሪካ እና የጫጩት ማስፈልፈያ በመገንባት ከራሳቸው አልፎ ለቀጣናው ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መኾናቸውንም ነው የተናገሩት።
ካላቸው ተሞክሮ በመነሳትም ሴቶች እና ወጣቶችም ሥራውን ሳይንቁ ቢሠሩበት ውጤታማ እንደሚያደርጋቸውም መክረዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ እና የእንስሳት ሃብት ክላስተር አስተባባሪ ግርማዬ ልጃለም የእንስሳት ሃብት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ነው ብለዋል።
ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ አልሚዎችን በክላስተር እንዲገቡ በማድረግ የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት እና ለመደገፍ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ዘርፉ ውጤት እየመጣበት መኾኑን በመገንዘብ ትላልቅ ባለሃብቶችም በዘርፉ ለመሠማራት ፍላጎታቸውን እያሳዩ ነው ብለዋል።

