(ታኅሣሥ 14/2018 ዓ.ም) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በሰሜን ጎጃም ዞን ከዱር ቤቴ ከተማ እና ከደቡብ አቸፈር ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሕዝብን የእሳት ቀንበር አሸክሞት ቆይቷል ብለዋል።
ለሕዝብ እንታገላለን የሚለው ቡድን ንጹሐንን የሚያግት፣ የሚገድል፣ የሃይማኖት አባቶችን የሚያዋርድ መኾኑን ተናግረዋል።
ጽንፈኝነትን እንዲያቆጠቁጥ፣ ግጭት እንዲነሳ እና እንዳይቋረጥ የሚያደርጉ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች አካላት መኖራቸውንም አንስተዋል።
በመንግሥት ቢሮ ውስጥ ተቀምጠው በጫካ ያለውን ቡድን የሚደግፉ እና መረጃ የሚያቀብሉ መኖራቸውን ተናግረዋል። ትምህርት ቤት እንዳይከፈት የሚቀሰቅሱ መምህራን እንዳሉም ገልጸዋል።
የታጠቀው ቡድን ከአማራ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላቶች ከሕወሐት እና ከሸኔ ጋር የሚሠራ ጠላት ነው ብለዋል። የታጠቀው ቡድን በእናቶች ማኅፀን እንጨት ሰዷል፤ ንጹሐንን በገላባ እሳት አቃጥሎ ገድሏል፤ በቡድን እናቶችን ደፍሯል፤ የሀገር መከለካያ ሠራዊትን ምግብ አበላሽ የተባለች እናትን ጡቷ ተቆርጧል፣ ይሄን ሰቆቃ በቃህ ማለት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በጫካ የሚገኘው ቡድን መንግሥት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ይጠቀም፣ አልጠቀምም ካለ ግን የተጠናከረ እርምጃ ሊወስድበት ይገባል ብለዋል።
ሕዝብ ተሳቆ እና ተጨንቆ እየኖረ ነው ያሉት ነዋሪዎቹ ተንቀሳቅሶ መሥራት እንዳልተቻለም ተናግረዋል።
ግጭትን የሚያባብሱ የመልካም አሥተዳደር እና ሌሎች ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ አንስተዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለሀገር ሰላም እና አንድነት የሚዋደቅ የሀገር መከታ መኾኑን ተናግረዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ማዳበሪያ አጅቦ እያመጣ አርሰን እንድንከርም ያደረገን ባለውለታችን ነው፤ ሰላማችን እና ልማታችንን ለማረጋገጥ መከላከያ ሠራዊትን መደገፍ አለብን ብለዋል።
ወደ ጫካ የወጡትን እየመከሩ የሰላም አማራጭን እንዲጠቀሙ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ግጭት በብዙ አከሰረን እንጂ አልጠቀመንም፤ ሰከን ብለን ሰላምን መመለስ አለብን ነው ያሉት።
ንብረታችን እየወደመ ያለው እኛው፣ እየተሰቃየን ያለነው እኛው፣ እየሞትን ያለነው እኛው፣ ሰላምን የምናመጣውም እኛው ነን ብለዋል።
ሰላምን የሚሰብኩ፣ እርቅ የሚያወርዱ የሃይማኖት አባቶች እንዳሉ ሁሉ ግጭትን የሚቀሰቅሱ እና ግጭትን የሚያራዝሙ አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች አሉ ነው ያሉት።
የሃይማኖት አባቶች ስለ እውነት እና ሰለ ሰላም እንዲሠሩም ጠይቀዋል። ሁሉም ተው ይሄ ነገር ከፍቷል፤ ሕዝብ አሰቃይቷል እያለ መምከር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን አቸፈር ወረዳ ክረምት ከበጋ ልማት የማይነጥፈበት፣ ሕግ አክባሪ እና ሰላምን ጠባቂ ሕዝብ የሚኖርበት መኾኑን ገልጸዋል።
ተቋማትን በመጠበቅ፣ ሰላሙን በማረጋገጥ ልማት የሠራ አካባቢ መኾኑንም አንስተዋል።
ሰላምን የሚያረጋግጠው የሰከነ እና እውነተኛ ውይይት መኾኑን ተናግረዋል። ከሕዝብ ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አንስተዋል።
ሰላምን በማረጋገጥ የሕዝብ ጥያቄዎችን መመለስ እና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
ውይይት እና ምክክር ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ ጠንካራ ሀገርን እንደሚያጸና አንስተዋል። ሰላምን የማረጋገጥ ኀላፊነት የሁላችንም ነው ብለዋል።
ሁለት ቦታ ላይ እየረገጡ ሕዝብ በስቃይ ውስጥ እንዲኖር የሚሠሩ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አስገንዝበዋል።
ልማት እንዲረጋገጥ ካስፈለገ መጀመሪያ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል፤ ልማት እንዲመጣ ከፈለጋችሁ የአካባቢያችሁን ሰላም ማረጋገጥ አለባችሁ ነው ያሉት።
የመልካም አሥተዳደር እና ሌሎች ችግሮችን ለማረም እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አዲሱ መሐመድ ዱር ቤቴን በጽንፈኛው ቡድን እንዳትወድም ያደረጋችሁት አስተዋጽኦ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል። ሕዝብ ዋናው ጉልበት ነው ያሉት አዛዡ በአንድነት ከተነሳችሁ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ትችላላችሁ ነው ያሉት።
በጉያችሁ እየደበቃችሁ እና መረጃ እያቀበላችሁ ሰላም ይምጣ ብትሉ አይመጣም ብለዋል።
በጫካ ያለው ዘራፊ ቡድን የውክልና ጦርነት የሚያደርግ፣ የታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪ እና ባንዳ መኾኑን ተናግረዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) ባለፉት ዓመታት ሕዝብን ዋጋ ያስከፈለ ችግር መፈጠሩን ተናግረዋል። እንደዋዛ የታጣውን ሰላም ለመመለስ መስዋዕትነት ተከፍሏል ነው ያሉት።
የመንግሥት ፍላጎት የታጣውን ሰላም በመመለስ፣ ሕዝቡ ወደ ልማት እንዲዞር፣ በነጻነት እንዲንቀሳቀስ፣ ተማሪዎች እንዲማሩ ማድረግ ነው ብለዋል። ጽንፈኛው ቡድን ግን የጭካኔ ተግባር የሚፈጽም፣ ሕዝብ እንዳያለማ የሚያደርግ መኾኑንም ተናግረዋል።
እየፈጸመው ባለው እኩይ ተግባር ከሕዝብ እየተነጠለ መኾኑን ገልጸዋል። ሕዝብን አደናግሮ የተነሳው ዘራፊ ቡድን የወጣበትን ሕዝብ እያሰቃየ መኾኑን ተናግረዋል።
እስካሁን ከደረሰው ጉዳት በመማር ለዘላቂ ሰላም መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የሚያሰቃያችሁን ቡድን በድፍረት መታገል፣ የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በተደረጉ ውይይቶች በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለዋል ብለዋል። የሰላም አማራጭን በማይቀበሉት ላይ እየተወሰደ ያለው የሕግ ማስከበር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። ዘላቂ ሰላም እንዳይመጣ የሚያደርጉት በግጭት የሚያተርፉት መኾናቸውንም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) አሁን ካለንበት አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለመሸጋገር የችግሩን መነሻ በማወቅ ማረም ያስፈልጋል ብለዋል። መመካከር፣ መደማመጥ እና መወያየት ለሰላም እሴት ግንባታ እንኳር ጉዳዮች መኾናቸውንም ተናግረዋል።
ለዘላቂ ሰላም በሀቅ ላይ ተመሥርቶ ከልብ መወያየት ያስፈልጋል ነው ያሉት። በውይይቱ የእውነት ሰላም እንደፈለጋችሁ ተረድተናል፤ ይሄን ግን ከንግግር ባለፈ መተግበር ያስፈልጋችኋል ብለዋል።
የሰላም ባሕል አለን ወይ ብላችሁ ራሳችሁን መጠየቅ አለባችሁ ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ የሰላም ባሕል ያለው ማኅበረሰብ ግጭትን፣ ሁከትን እና ብጥብጥን የሚጠየፍ፣ አንድነትን የሚያጠናክር፣ ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
የሰላም ባሕል ግንባታ ሐቅ ላይ ተመሥርቶ እውነተኛ እርቅ ማድረግ መኾኑን ተናግረዋል። ለሰላም ባሕል ግንባታ ከተዘጋጃችሁ አሁን ያለውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት ማጽናት ይጠበቅባችኋል ነው ያሉት።
“ሕዝብ ሐቀኛ ውይይት እና ምክክር ካደረገ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ይችላል” ብለዋል። ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎች መደረጋቸውን እና በርካቶች የሰላም አማራጭን መቀበላቸውን ተናግረዋል።
ከሰላም አማራጭ ጎን ለጎን የሕግ ማስከበር ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። ችግር በሚያባብሱ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም ተናግረዋል። በጫካ ያለው ቡድን ሃሳቡ ጽንፈኝነት፣ ተግባሩ ጭካኔ እና የጠላት ተላላኪ መኾኑን ገልጸዋል።
ከሕዝብ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር የሚላላክ ቡድን ለሕዝብ ሊጠቅም እንደማይችልም ተናግረዋል። ለዘላቂ ሰላም እውነት ላይ ቆሞ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
የዱር ቤቴ – ቁንዝላ – ሻውራ – ፍንጅት- ገለጎ -ገንዳ ውኃ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት እና ሌሎች የልማት ሥራዎች እንዲጠናቀቁ ሰላማችሁን መጠበቅ ያስፈልጋችኋል ነው ያሉት።

