በምዕራብ ጎንደር ዞን 990 ሺህ ኩንታል ሰሊጥ ምርት ተሰበሰበ

በምዕራብ ጎንደር ዞን በመኸር ወቅት በሰሊጥ ከለማው መሬት 990 ሺህ ኩንታል ምርት ተሰብስቧል

በምዕራብ ጎንደር ዞን በመኸር ወቅት ከለማው መሬት ከ990 ሺህ ኩንታል በላይ የሰሊጥ ምርት መገኘቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ደግሰው አየለ እንደገለጹት፤ የሰሊጥ ምርቱ በ2017/18 የምርት ዘመን ከለማው 119 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተገኘ ነው።

ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ሰሊጥ የጥራት ደረጃውን ጠብቆ እንዲሰበሰብም ባለሙያዎች ድጋፍ ማድረጋቸውን አቶ ደግሰው አስረድተዋል።

በምርት ሂደቱ ከ46 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እና ከ500 በላይ ባለኃብቶች በተሻለ አስተራረስ እና በቴክኖሎጂ ታግዘው መሥራታቸው ለተገኘው ውጤት አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።

ከተሰበሰበው ምርት ውስጥ 856 ሺህ ኩንታል የሚጠጋው በአርሶ አደሮች የተመረተ ሲሆን፣ ቀሪው በባለሀብቶች መሆኑንም ገልጸዋል።

በመተማ ወረዳ ሽመለ ጋራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አስማማው ዋሴ፤ በ2017/18 የምርት ዘመን ሶስት ሄክታር መሬት በሰሊጥ በማልማት 19 ኩንታል ሰሊጥ ማግኘታቸው ገልጸዋል።

ካገኙቱም የሰሊጥ ምርት ውስጥ አንድ ኩንታል በ13 ሺህ ብር በመሸጥ ባለፈው ዓመት ካገኙት በተሻለ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ካለሙት መሬት 84 ኩንታል ሰሊጥ ማግኘታቸውን የገለጹት ደግሞ በመተማ ወረዳ የደለሎ የእርሻ ልማት ጣቢያ ባለሃብት ወኪል አቶ እንደሻው ማሩ ናቸው። ምርቱ አሁን ባለው የሰሊጥ ዋጋ ተጠቃሚ ያደርገኛል ብለዋል።

በመኸር ወቅት ከተሰበሰበው የሰሊጥ ምርት ከ800 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነው ወደ ማዕከላዊ ገበያ የሚቀርብ መሆኑን የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታውቋል።

በእስካሁኑ ሂደትም ከ200 ሺህ ኩንታል በላይ ሰሊጥ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ ተችሏል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን ባለፈው ዓመት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰሊጥ ተመርቶ ለውጭ ገበያ መቅረቡን ከግብርና መምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top