የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ እና የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በሙስና ወንጀል ምርመራ እና ክስ አመሠራረት የቅንጅት ሥራ ላይ ውይይት እያደረጉ እንደሚገኙ ተገልጿል።
በውይይቱ የተገኙት የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም እንዳሉት፦ የሕዝብን ደኅንነት ለማረጋገጥ፣ የመንግሥት እና የሕዝብ ሀብት ለታለመለት አላማ እንዲውል መከታተል የፍትሕ ተቋማት ሃላፊነት ነው ብለዋል።
ከወንጀል መከላከል ጀምሮ በምርመራ፣ በክስ፣ በክርክር፣ ጥፋተኞችም ታርመው ጥሩ ዜጋ ኾነው እንዲወጡ የፍትሕ እና የፖሊስ ተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር እንደሚጠይቅም አንስተዋል።
አሁን ላይ በክልሉ አስጊ እየሆነ የመጣውን የሙስና ወንጀል ለመከላከል እና አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ የፍትሕ ተቋማቱ ተቀናጅተው እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ትውልድን በሥነ ምግባር፣ ተቋምን ደግሞ በአሠራር በማጠናከር በክልሉ ያለውን የሙስና ወንጀል መከላከል የሁሉም ድርሻ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር) በበኩላቸው፦ ሙስና የጥቂቶች መበልጸጊያ ነው ብለዋልል።
በክልሉ የሚታየውን ብልሹ አሠራር እና ሙስና በመከላከል የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ አንዱ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው።
ለዚህ ደግሞ ፍትሕ ቢሮ እና ፖሊስ ተቀናጅተው እየሠሩ ነው። የፖሊስን የምርመራ አቅም የማጎልበት ሥራም እየተሠራ ነው ብለዋል።

