(ታሕሳስ 08/2018 ዓ.ም) የአማራ ክልል እና ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ለአምስት ዓመታት የሚተገበር የልማት መርሐ ግብር ስምምነት ተፈራርመዋል።
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በክልሉ የረጅም ጊዜ የልማት አጋራችን ነው ብለዋል።
ድርጅቱ በክልሉ የልማት እንቅስቃሴ ለረጅም ጊዜ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ተናግረዋል።
አሁንም በክልሉ በበቂ ሁኔታ በልማት ያልተደገፉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ እና ተደራሽ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
መርሐ ግብሩ የሚተገበርባቸው ዘርፎች በጥንቃቄ የተለዩ መኾናቸውንም ነው የገለጹት።
በዚህ በቅት አማራ ክልልን መደገፍ የተለየ ያደርገዋል ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ።
ቀደም ሲል በሰሜኑ ጦርነት እና አሁንም በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በርካታ የተጓተቱ ሥራዎች መኖራቸውን አንስተዋል።
ከተስተጓጎሉት ሥራዎች መካከል ትምህርት አንዱ ነው ብለዋል። በተለይም ሴቶች እና ሕጻናት የችግሩ ሰለባ መኾናቸውንም አንስተዋል።
ይህንን መሠረት በማድረግ ወርልድ ቪዥን በትምህርት ላይ መሥራቱ ትልቅ ትርጉም ይሰጠዋል ነው ያሉት።
አካታች ልማት እንዲመጣ በተለይም ሴቶች እና ሕጻናት ላይ ለመሥራት የሚደረገው ጥረትም የሚበረታታ ነው ብለዋል።
በክልሉ በርካታው ማኅበረሰብ በአመጋገብ ላይ ችግር የሚስተዋል በመኾኑ በግብርናው ዘርፍም በተለይ ሥነ ምግብ ላይ ለመሥራት የተያዘው መርሐ ግብር የሚደገፍ መኾኑን ነው የገለጹት።
የተሻለ የሥነ ምግብ እሴት ያላቸውን ምርቶች ላይ ትኩረት መደረግ እንደሚገባ አንስተዋል።
በመስኖ ልማት እና በሌሎች ምርታማነትን በሚጨምሩ አሠራሮች ላይ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተናግረዋል።
አብዛኛው ማኅበረሰብ በገጠር የሚኖር በመኾኑ መዋቅራዊ ሽግግር ሊያመጣ በሚያስችል አሠራር ላይ በስፋት መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ድጋፉ የሚያሻግር መኾን አለበት ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በኢኮኖሚ ነጻ መውጣትን የሚያረጋግጥ መኾን አለበት ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ በአምራች ዘርፎች እና እሴት በሚጨምሩ የልማት ዘርፎች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ምርታማ ለመኾንም የሰው ኀይል ልማት ላይ ማተኮር እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
በጤናው ዘርፍም ድጋፉ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለአካባቢ የተስማማ ልማት መሠረት አድርጎ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በክልሉ ካሉት ቁልፍ አምስት ደጋፊዎቻችን ውስጥ አንዱ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል።
ሥምምነቱ በሕጻናት ጥበቃ፣ በአመጋገብ ሥርዓት እና በትምህርት ላይ ትኩረት አድርጎ ለመሥራት ዓላማ ያደረገ ነው።

