“ሀገር እና ሕዝቤን እወዳለሁ የሚል ሁሉ ከጥፋት መንገድ ፈጥኖ ይውጣ” አቶ ይርጋ ሲሳይ

ከፍተኛ መሪዎች ከሀብሩ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር በመርሳ ከተማ ተወያይተዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሐ ደሳለኝ፣ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ፣ የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መሪ ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ እና ሌሎችም የዞን እና የክልሉ የሥራ ኀላፊዎች በመድረኩ ላይ ተገኝተዋል።

የአካባቢው የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አበጋሮች እና ወጣቶች በውይይቱ ተሳትፈዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ የአማራ ክልል ሕዝብ ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር በመቆም ሀገር የገነባ ባለ አሻራ ነው ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሚታዘዙ ታጣቂዎች ለሀገር እና ለሕዝብ የቆሙ በመምሰል የሀገርን ታሪክ የማይመጥን ጥፋት እየፈጸሙ ሕዝብን አሳዝነዋል ነው ያሉት።

“ሀገር እና ሕዝቤን እወዳለሁ የሚል ሁሉ ከጥፋት መንገድ ፈጥኖ ይውጣ” ሲሉም አስገንዝበዋል።

“የሕዝብ ኩራቱ ማልማቱ ነው” ያሉት አቶ ይርጋ ግጭት እና ጦርነትን መጠየፍ፣ በታታሪነት ማልማት እና ረብ ያለው ተግባር አከናውኖ አንገትን ቀና አድርጎ መራመድ እንደሚገባ መክረዋል።

ስም እስከወዲያኛው ነው፤ ጀግና እና ባለታሪክ ሕዝብን መበደል መጥፎ ስም ተክሎ ማለፍ ነው ብለዋል።

የዚህ መጥፎ ስም ባለቤት ላለመኾን ከበደል መውጣት ግድ ይላል ብለዋል አቶ ይርጋ።

የጥፋት መንገድ በቃኝ ብለው ከጫካ የተመለሱት ሁሉ ሰላምን መርጠዋልና ወንድሞቻችን እና ልጆቻችን ናቸው፤ እንደግፋቸዋለን ብለዋል።

የሰላም ጥሪውን ገፍተው አሁንም በጥፋት መንገድ የቀጠሉትን ግን ሰላም ወዳድ የኾነ ሁሉ በጋራ ቁሞ ሊያወግዛቸው እና ለደህንነቱ ሲል አሳልፎ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ሕዝብ ግጭት በቃኝ እያላቸው፣ መንግሥትም ይቅርታ እያደረገላቸው አሻፈረኝ የሚሉት የአማራነትንም ኾነ የኢትዮጵያዊነትን እሴት ያልተላበሱ፣ የሕዝብ ስቃይም ደንታ የማይሰጣቸው መኾናቸው በግልጽ መታወቅ አለበትም ብለዋል።

እነዚህ አካላት እንደ አማራ ክልል ሕዝብ አንድ እንዳይኾን የሀገር ሉዓላዊነትም እንዲጣስ የሚሠሩ መኾናቸውን በመረዳት በጋራ ታግሎ ማስተካከል እንደሚገባም ጠቁመዋል።

“በመሸፋፈን የሚመጣ ሰላም የለም” ያሉት አቶ ይርጋ አጥፊን በስሙ እየጠሩ መታገል እና ለሰላም በተግባር መቆም እንደሚጠበቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ላኪም ኾነ ተላላኪ ጠላቶች ሞኞች ናቸው፤ ለጊዜው የክልሉን ሕዝብ ለማጎሳቆል የሚችሉ መስሏቸው ነበር፤ አሁን ግን ሕዝብ በቃኝ ብሏቸዋል ነው ያሉት አቶ ይርጋ።

ሕዝብን እየበደሉ መኖር አይቻልምና በደልን ፈጥኖ ማቆም፤ ድርጊቱንም መጥላት ግድ ይላል ብለዋል።

በግጭትና ጦርነት ውስጥ ሀብት ለመፍጠር መፈለግ ጤነኝነትም ደንነትም አይሰጥም፣ ይልቁንም ሰላምን አስፍኖ ሠርቶ መለወጥን መመኘት ይበጃል ነው ያሉት።

ብቸኛው አማራጭ ሰላምን መምረጥ ነው፤ ሰላምን የሚጠላ አካል ሲፈጠር ግን መንግሥት ከየትኛውም ጊዜ በላይ ሕግ በማስከበር የሕዝብን ደኅንነት ያስጠብቃል ብለዋል።

“የሚበልጥብን የሀገር እና የሕዝብ ሕልውና ነው፤ ሀገርን እና ሕዝብን የማይመጥን ተግባር የሚያራምድ ማንኛውም አካል ቢኖር መንግሥት በዝምታ እንደማያልፈው፤ ሕዝብም እንደማይታገሰው ይወቅ ብለዋል አቶ ይርጋ።

የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር “ታጣቂዎች እያጠፉም ሸፋፍኖ በያዛቸው ሕዝብ ላይ ሌላ የውጭ ጠላት ስበው እያመጡበት ነው” ብለዋል።

በዞኑ በርካታ ታጣቂዎች ሰላምን መርጠው ቢገቡም አሁንም ድረስ ከጫካ ያልወጡም አሉ ብለዋል።

የምትሸመግሉ አባቶች እና የታላቅ ምክር የምትቀበሉ ወጣቶች ትመሰገናላችሁ፤ አሁንም ቢኾን ለሰላም የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top