“የሃይማኖት አባቶች ሚና እና ተልዕኮ ሰላምን መስበክ ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

(ታኅሣሥ 07/2018 ዓ.ም) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከምዕራብ ጎጃም ዞን የሃይማኖት አባቶች ጋር በፍኖተ ሰላም ከተማ ተወያይተዋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ የክልሉ መንግሥት በምዕራብ ጎጃም ዞን በርካታ የልማት ሥራዎችን ማስጀመሩን ተናግረዋል።

በልማት የተሰጠውን እድል ለመጠቀም ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የሰላም መደፍረሱ ታላላቅ የልማት ሥራዎች እንዲዘገዩ ማድረጉን እና ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት የሕዝብን ጥያቄዎች በአግባቡ እየፈታ መኾኑን ገልጸዋል። ልማት እንዳይሠራ፣ ተማሪዎች እንዳይማሩ የሚያደርጉትን በድፍረት ማውገዝ አለባችሁ ነው ያሉት።

የሃይማኖት አባቶች የሚጠበቅባቸውን የሰላም መሪነት መጠቀም እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

በድፍረት በመምከር እና በመገሰጽ ታጣቂዎች ለሰላም ዝግጁ እንዲኾኑ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።

የእውነት አምላክ ተከታዮች እና ሰባኪዎች እንደኾናችሁ ሁሉ እውነት ላይ ቆማችሁ ለሰላም መሥራት አለባችሁ ነው ያሉት። ከዚህ በላይ የሕዝብ ስቃይ እና እንግልት ሊያቆም ይገባል ብለዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ባለፉት ዓመታት ንጹሐን በግፍ የሚገደሉበት፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የማይከበሩበት ሁኔታ ተፈጥሮ ቆይቷል ነው ያሉት።

ሰላም በምላስ ጫፍ ብቻ አትመጣም፤ እውነት ላይ በመቆም እና ሰላምን በተግባር መኖር ሲቻል ነው ሰላም የሚረጋገጠው ብለዋል።

እውነተኛ ሐዋርያዊነታቸውን በመወጣት ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የሕዝብን ሥነ ምግባር በመገንባት ረገድ የሃይማኖት ተቋማት ቀዳሚዎች መኾናቸውን ተናግረዋል።

ይህን የቆዬ ታሪክ እና ታላቅነት ለማስቀጠል መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት። ግጭትን በማውገዝ ሰላምን እንዲያረጋግጡም ጠይቀዋል።

የሃይማኖት አባቶች ሚና እና ተልዕኮ ሰላምን መስበክ ነው ብለዋል። ራሳቸውን ከፖለቲካ እሳቤ በማጽዳት በሃይማኖቱ አስተምህሮ ወሰን ውስጥ ተልዕኳቸውን እንዲፈጽሙም ጠይቀዋል።

በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የሚንቀሳቀሱ እና ሃይማኖትን የማይወክሉ አባቶችን ማውገዝ እና መምከር እንደሚገባቸውም አመላክተዋል።

የሃይማኖት አባቶች ግፍን በግልጽ ማውገዝ እና መገዘት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

በየገዳማቱ፣ በየአብያተ ክርስቲያናቱ እና በየመስጊዶቹ ሰላምን በመስበክ ጎጃምን ወደ ነበረበት ክብሩ እንዲመለሱም አሳስበዋል።

ተባብረን ሰላምን ለማረጋገጥ እንነሳ፤ እስካሁን ለሰላም የሠራችሁትን የሃይማኖት አባቶች እናመሰግናለን፤ ነገር ግን በቂ አይደለም አሁንም መሥራት ይጠበቅባችኋል ነው ያሉት። ሰላምን ለማረጋገጥ በአንድነት እንዲሠሩም ጠይቀዋል።

የክልሉ መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ለሰላም በሰጠው አማራጭ በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን መቀበላቸውን ገልጸዋል። የሰላም አማራጭ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስተዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top