በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምሥራቅ ደንቢያ ወረዳ በዘላቂ ሰላም ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ ከምሥራቅ ደንብያ እና ከቆላድባ ከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
በወረዳው ተፈጥሮ በነበረው የሰላም እጦት ምክንያት የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ተዘግተው መቆየታቸው ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ዳርጎ መቆየቱን በውይይቱ ተነስቷል።
በወረዳው ከዚህ ቀደም እገታ እና ግድያ ተበራክቶ እንደነበር ያነሱት ተሳታፊዎቹ አሁን ላይ አንጻራዊ መረጋጋት መኖሩን ገልጸዋል።
ዘላቂ ሰላም የሚመጣው መሰል የሰላም ውይይቶችን ከማድረግ ባሻገር ተግባር ተኮር የሰላም ማስፈን ሥራ በመሥራት እንደኾነም በውይይቱ ተጠቅሷል። ለመፍትሔው በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው የተጠቀሰው።
የምክክሩ ተሳታፊዎች የታጠቁ አካላት የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ የበኩላቸዉን እየተወጡ እና በቀጣይም እንደሚወጡ አንስተዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ ጫካ የገቡ አካላት በሰላም እጅ እንዲሰጡ በተሠራዉ ተግባር ለውጥ እየመጣ መኾኑን ተናግረዋል።
በኅብረተሰቡ የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሠራ ሥለመኾኑም ተናግረዋል።
የወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
ለሀገር ሰላም መጽናት ተግተው እየሠሩ መኾኑን የተናገሩት በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሥራ ኀላፊ የኾኑት ኮሎኔል ዘሪሁን ተረፈ በበኩላቸው ሰላም የማስፈን ሥራው የሁሉም ድርሻ መኾን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
አሁን ላይ ያለውን ተስፋ ሰጭ የሰላም ተግባር አጠናክሮ ለማስቀጠል ተግቶ መሥራት ይጠይቃልም ብለዋል።
“ጥፋት በጥፋት አይመለስም” ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ ናቸው።
የታጠቁ አካላት ለሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ በትኩረት እየተሠራ እንደሆነም ገልጸዋል።
ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚሠራው ተግባር የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) የሃይማኖት አባቶች የአማራ ሕዝብ መከራ ውስጥ እንዳይገባ ተግተው እንዲሠሩ አሳስበዋል።
በክልሉ በታጠቁ ኃይሎች እየተካሄደ ያለው እገታ እና የግድያ ተግባር ከአማራ ሕዝብ ባሕል ያፈነገጠ ነው ያሉት ኀላፊው በእኩይ ዓላማ የተሰማሩ ዜጎችን መታገል ይገባል ብለዋል።
“ታሪካዊ ጠላቶች በሸረቡት ሴራ ላለመጠለፍ በጋራ መሥራት ያስፈልጋልም” ነው ያሉት።
ከሰላም ውጭ ያለው አማራጭ አውዳሚ በመኾኑ ኅብረተሰቡ ለዘላቂ ሰላም ተግቶ እንዲሠራም መልዕክት አስተላልፈዋል።

