ታኅሣሥ 07/2018 ዓ.ም) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከምዕራብ ጎጃም ዞን የሃይማኖት አባቶች ጋር በፍኖተ ሰላም ከተማ እየተወያዩ ነው።
በውይይቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችም ተገኝተዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ ሰላምን ለማረጋገጥ ከሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል። በተደረጉ ውይይቶችም ለውጥ መገኘቱን ገልጸዋል።
ግጭት የሰውን ሕይዎት የሚቀጥፍ ነው ያሉት አሥተዳዳሪው የሃይማኖት አባቶች በየሃይማኖት ተቋማት ሰላምን እየበሰኩ ነው ብለዋል። ሰላምም እንዲመጣ እያስተማሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ከዚህ የበለጠ ስለ ሰላም መስበክ እና ማስተማር እንደሚጠበቅም ተናግረዋል። የሃይማኖት አባቶች ሚና አሁን ካለው የላቀ እና የበለጠ መኾን እንደሚገባውም ተናግረዋል።
የአካባቢው ሰላም እንዲረጋገጥ፣ በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ አባታዊ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
መንግሥት ሰላምን ለማረጋገጥ ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር የሃይማኖት አባቶች የራሳቸውን ኀላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት።
የሃይማኖት አባቶች ከልብ ከመከራችሁ እና ከገሰጻችሁ ሰላምን ማረጋገጥ ይቻላል ነው ያሉት። ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ፣ ማኅበራዊ እንቅስቃሴው በነጻነት እንዲከናወን ለሰላም መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ሰላም ከላይ የተለካ መለኮታዊ ጸጋ እና ቃል መኾኑን ተናግረዋል።
ሰላም ለሃይማኖት አባቶች የዕለት ከዕለት ተግባር እና ሃይማኖታዊ ተልዕኮ መኾኑን ገልጸዋል። የሃይማኖት አባቶች ይሄን የዕለት ከዕለት ተግባራቸውን መፈጸም እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
“ሰላም ሁልጊዜ እርቅን፣ መቻቻልን እና ይቅር ባይነትን ይፈልጋል” ብለዋል።
ሁሉም ሃይማኖቶች ለጸሎት ሲነሱ ሰላምን ይሰብካሉ ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ችግሮች እንዳሉ ነው የተናገሩት።
ከእናንተ ጋር የምንወያየው ልጆቻችሁ ሰላምን እንዲመርጡ፣ በጎቻችሁ ወደ ሰላም እንዲመጡ እና ከሰላም ትሩፋት እንዲጠቀሙ ነው ብለዋል። ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱ በሰላም እንዲከወን ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ግብረ ገብነትን ለልጆች ማስተማርን እንደሚገባም ተናግረዋል። ከግብረ ገብነት እና ከእሴት እየወጣ ያለውን ትውልድ ማስተማር ከሃይማኖት አባቶች እንደሚጠበቅም አንስተዋል።
ሰላምን ለማረጋገጥ የሃይማኖት አባቶች እውነተኛ ሚናቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ነው የገለጹት። በውይይት የየደርሻችንን ወስደን ለሰላም መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
ከሃይማኖት አባቶች እውነተኛ የሰላም ሐዋርያነት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል ሲል የዘገበው አሚኮ ነው።

