የሌማት ትሩፋት ስኬት ምሳሌ ወጣቶች!

(ታኅሣሥ 07/2018 ዓ.ም) በአማራ ክልል የእንሥሣት ሃብትን በማልማት ለሌማት ትሩፋት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት እየተሠራ ይገኛል።

ይርጋ አያሌው እና ጓደኞቻቸው የኅብረት ሽርክና ማኅበር ስድስት አባላት ያሉት በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኝ የዶሮ ርባታ ማኅበር ነው።

የማኅበሩ አባል ወጣት ብርሃን ሺበሺ የዶሮ ርባታ ሀሳብ የመጣላቸው አረብ ሀገር ሄደው ተቀጥረው ሲሠሩ ዶሮ ሲያረቡ በማየታቸው መኾኑን ይናገራል።

ከዚያ ጊዜ ጀምረን በስደት ነጻነታችንን አጥተን ከምንኖር ይልቅ በሀገራችን መሥራት እንዳለብን ወስነን ሥራ ጀመርን ይላል። በአሁኑ ወቅት ከጓደኞቹ ጋር እየሠሩት ባለው ሥራም ውጤታማ እና ደስተኛ መኾናቸውን ገልጿል።

የማኅበሩ ምክትል ሥራ አሥኪያጅ ወጣት ይርጋ ወሰንየለህ ለሥራ ፍለጋ ወደ አረብ ሀገር ሄዶ እስከ መታሰር የደረሰ እንግልት እና ስቃይ እንደደረሰበት ነው የሚናገረው።

ይርጋ እና ጓደኞቹ ባጋጠማቸው እንግልት ቁጭት ውስጥ በመግባት ወደ ሀገራቸው ተመልሰው የዶሮ ርባታ ሥራ መጀመራቸውን ይናገራሉ።

ወጣቱ እንደገለጸው በመጀመሪያ በ1 ሺህ 500 ዶሮ ነበር ሥራቸውን የጀመሩት። በግል የመሥሪያ ቦታ ተከራይተው ሲሠሩ ቆይተዋል። በሂደትም የመንግሥት ቦታ ተመቻችቶላቸዋል። ሥልጠናም ተሰጥቷቸዋል።

እንሥሣት ፍቅር እና እንክብካቤ ይፈልጋሉ የሚለው ወጣቱ በተለይም ለዶሮ ርባታ ሥራ ቁርጠኝነትን፣ ክትትል ማድረግን፣ አብሮ መዋል ማደርን፣ አለመሠልቸትን አስቦ ከተሠራ ውጤታማ መኾን ይቻላል ይላል።

አሁን ላይ 7 ሺህ 500 ዶሮዎች አሏቸው። በቀን በአማካይ ከ7 ሺህ በላይ እንቁላል እያመረቱ ለገበያ ያቀርባሉ። 6 ሚሊዮን ብር ካፒታል መድረሳቸውንም ገልጸዋል። የእንቁላል ምርቱን እስከ አዲስ አበባ ድረስ ይልካሉ።

ማኅበሩ ሞዴል ኾኖ በክልል ደረጃ ተሸላሚ መኾን እንደቻሉም ነው የገለጸው። በቀጣይም በስጋ ዶሮ ምርት በሥፋት በመሥራት ወደ ውጭ ለመላክ እቅድ እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ወጣቶቹ በሀገር ላይ ሠርቶ መለወጥ እንደሚቻል በተግባር አይተዋል። ሌሎች ወጣቶችም በየአካባቢያቸው ሠርተው መለወጥ እንደሚችሉ ምክራቸውን ሰጥተዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ታሪኳ እሸቱ በዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በዶሮ ርባታ ዘርፍ ለተሰማሩ ወጣቶች ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ፣ ሥልጠናዎችን በመሥጠት፣ በመድኃኒት አቅርቦት እና የሕክምና ክትትል በማድረግ ድጋፍ እያደረጉ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።

በከተማዋ በአንድ ቀን ጫጩት ማሳደግ የተሰማሩ 21 ኢንተርፕራይዞች መኖራቸውን ገልጸዋል። በእንቁላል ጣይ ዶሮ ርባታም በስፋት እየተሠራበት ነው ብለዋል።

በቀን 125 ሺህ እንቁላል እየተመረተ እና ለገበያ እየቀረበ ስለመኾኑም ጠቁመዋል ሲል የዘገበው አሚኮ ነው።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top