የግብርና ሚኒስቴር በድጋፍ ያገኛቸውን ከ2 ቢሊዮን በላይ ብር የሚገመቱ የግብርና ግብዓቶች ለፌደራል ተቋማት፣ ለከተማ አስተዳደሮችና ለክልሎች አስረክቧል።
የግብርና ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት፦ እነዚህ ግብዓቶች የግብርና ትራንስፎርሜሽን ለማሳካት ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል።
በድጋፍ የተገኙት ግብዓቶች 267 የመስክ ተሽከርካሪዎች፣ 1 ሺህ 854 ሞተር ሳይክሎች፣ 2 ሺህ 289 የውሃ መሳቢያ ፓምፖች እና የጥገና ቱል ቦክሶች መሆናቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ድጋፉ የተገኘው ከዓለም ባንክ፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች መሆናቸውን ጠቁመው፦ የተሰጡ ግብዓቶች ለሚመለከታቸው ወረዳዎች በፍጥነት በማድረስ የሚጠበቀው ውጤት ለማግኘት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ ከ38 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር የሚታረስ መሬት እንዳላት የጠቀሱት ሚኒስትሩ፦ ይህን በመጠቀም የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
በሀገሪቱ የግብርና ብድር ለአርሶ እና አርብቶ አደሮች የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን፣ ይህም አርሶ አደሩን ከበሬ በመነጠል በመካናይዜሽን መንገድ ግብርና ማጎልበት እንዲችል ያለመ ነው ብለዋል።
እንደ ሀገር የምግብ ዋስትና ብቻ ሳይሆን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ መስራት ይገባልም ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

