በምስራቅ ደምቢያ እና በቆላድባ ከተማ አካባቢ ታጥቀዉ በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂ ሃይሎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለዉ ገቡ።

ይህ የሰላም ሂደትም ክልሉን የማጠናከር እና አንድነትን ከመገንባት በኩል ትልቅ ምዕራፍ ነዉ።

በአቀባበል ፕሮግራሙ የተገኙት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና መሬት መምሪያ ኃላፊ አቶ አላምረው፥ የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ማህበረሰባቸው ለመካስ መምጣታቸው ትልቅ ብስራትና የብስለት ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።

አሁንም በጫካ ያሉ ጓደኞቻቸው እንዲገቡ ለማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነታችሁን ልትወጡ ይገባል ብለዋል።

የሰላም ጥሪውን ለተቀበሉ አካላትም አስፈላጊውን እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው አብራርተዋል።

ከሁለት ዓመት በላይ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የቀድሞ ታጣቂዎችም በበኩላቸው፥ “ከዚህ በፊት የህብረተሰቡን ሰላምና ህይወት ከማወክ ያለፈ ምንም አላመጣንም።

በመሆኑም ትግላችን የተሳሳተና ውጤት የሌለው እንደነበር አሁን ተገንዝበናል።

ማህበረሰቡ ያለበትን ችግር በአግባቡ በመረዳት በተሳሳተ አቅጣጫ መውጣታችን ስህተት መሆኑን አውቀን ተመልሰናል” ሲሉ ያለፈውን ተግባራቸውን በቁጭት መልክ ተናግረዋል።

በተደረገላቸው እንክብካቤና አቀባበል እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ለመንግስትና ለማህበረሰቡ ምስጋና አቅርበዋል።

በዚህ አቀባበል ፕሮግራም ላይ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና መሬት መምሪያ ኃላፊ አቶ አላምረው አበራ፣ የ62ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ኮሎኔል ዘሪሁን ተረፈን ጨምሮ የወረዳውና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች መገኘታቸውን ከዞኑ ኮሙኒኬሽን መመሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top