(ታሕሳስ 5/2018 ዓ.ም) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሚሊሻ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በከተማ አሥተዳደሩ ለሚገኙ የሰላም አስከባሪ ኀይሎች ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።
ሥልጠናው ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ሂደት ግዳጅ እና ተልዕኮዎችን የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችል መኾኑ ተገልጿል።
በሥልጠና ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የተገኙት የአማራ ክልል ሚልሻ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ገደቤ ኀይሌ የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ ኀይሎች ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ሂደት ሙያዊ ኀላፊነታቸውን መወጣታቸውን አስታውቀዋል።
በተፈጠረው የሰላም እጦት ሳቢያ ብዙዎች ከኀላፊነታቸው ሲርቁ ችግርን ተቋቁሞ መቀጠል የቻለ ሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ ኀይሎች ናቸው ብለዋል።
ጠላታችን ድህነት ነው ብለን እናምናለን ያሉት የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ ድህነትን ለማጥፋት ለሰላም ከምንጊዜውም በላይ ተግቶ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሥነ ምግባር የታነጸ፣ መከባበር እና መደማመጥን ያስቀደመ “ከእኔ በፊት ሕዝቤ ይብለጥ” የሚል የሰላም አስከባሪ ኀይል ለመገንባት የሚያስችል ሥልጠና መኾኑንም አቶ በሪሁን ጠቁመዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኮሎኔል አጋዬ ታደሰ በበኩላቸው “የተረጋጋች ከተማ በመፍጠር ሕዝባችንን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ መሥራት ይጠበቅብናል”ነው ያሉት።
የሕዝብን ሰላም የሚያጸና ሰላም አስከባሪ መገንባት ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ አለልኝ ዓለም ናቸው።
የሥልጠናው ተሳታፊ የሰላም አስከባሪ ኀይሎች ሥልጠናው የመፈጸም አቅማቸውን እንደሚያጎለብትላቸው ገልጸው ከሥልጠና በኋላ የቀደመ ጥንካሬያቸውን አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉም ተናግረዋል።

