(ታሕሳስ 6/2018 ዓ.ም) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምዕራብ ጎጃም ዞን በየደረጃው ከሚገኙ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) “የቀውስ ጊዜ መሪ ኹኔታዎችን የሚቋቋም፣ የሚወስን፣ የሚታመን እና ችግሮችን ተንትኖ መፍትሔ የሚያመላክት ነው ብለዋል።
መሪዎች የሕዝብ እና የመንግሥት ግንኙነት እንዲጠናከር መሥራት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
“እናንተ የቀውስ ጊዜ መሪዎች ናችሁ፤ ቀውሱን የምታረጋጉ፤ የመፍትሔ ሃሳብ የምታቀርቡ ናችሁ፤ ይሄን በመረዳት መሥራት ይጠበቅባችኋል” ብለዋል። ምዕራብ ጎጃም የጠላት የስበት ማዕከል ነበር ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ የጠላትን የስበት ማዕከል በመምታት አንጻራዊ ሰላም ተፈጥሯል ነው ያሉት።
አንጻራዊ ሰላም እንዲፈጠር ላደረጉ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ የጸጥታ ኃይል እና ቆራጥ መሪዎች
ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
የጎጃምን ሰላም ማረጋገጥ የጂኦ ስትራቴጂን ማስተካከል፤ የምግብ ለዓላዊነትን ማረጋገጥ እና በዓባይ ፖለቲካ የሚሠራውን ሴራ በበላይነት መወጣት ነው ብለዋል። ይሄን በመረዳት ለአካባቢው ሰላም በትኩረት እንዲሠሩ አሳስበዋል።
የትምህርት ስብራቱን ለመጠገን እየተሠራ ያለው ሥራ የሚበረታታ መኾኑን ተናግረዋል። የተጀመረውን የልማት ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል። ሕዝቡ የችግሩን መነሻ እና የመፍቻ መንገድ ላይ የጠራ ሃሳብ እንዲይዝ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንዲሠሩም አመላክተዋል።
ዛሬም ድረስ የጠላት ፕሮፖጋንዳ የወሰደው የኅብረተሰብ ክፍል እንዳለ ተናግረዋል። የጸጥታ ችግሩን ለመፍታት ሕዝብ የጠራ ሃሳብ እንዲይዝ ማድረግ እና ለመፍትሔው በጋራ እንዲሠራ ማድረግ እንደሚገባቸው ነው የገለጹት።
መሪዎች ራሳቸውን ከጽንፈኝነት አስተሳሰብ ማራቅ እና ለሕዝብ ታማኝ ኾነው እንዲሠሩም አስገንዝበዋል። የጎጃም ሕዝብ የሚታወቅበት ትርፍ አምራችነት፤ ሀገርን በምርት መቀለብ እና ችግርን በውይይት መፍታት ነው ብለዋል።
ሕዝቡን ከሥነ ልቦና ጫና ማውጣት እና ለሰላም በአንድነት እንዲነሳሳ ማድረግ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። ሕዝብን ለሰላም በአንድነት በማስነሳት ልጆች እንዲማሩ፣ በሰላም እንዲንቀሳቀሱ እና በልማት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ጽንፈኛው የባዕዳንን ተልዕኮ ተሸክሞ የባንዳነት ሥራ የሚሠራ ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ የባዕዳንን ተልዕኮ እየሠራ ያለውን ጽንፈኛ በማጽዳት አስተማማኝ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን የላቀ አስተዋጽኦ
ለማስቀጠል አስተማማኝ ሰላምን ማረጋገጥ ታሪካዊ ኀላፊነት መኾኑንም ተናግረዋል።
ሰላምን በማረጋገጥ ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል። ሕዝብን እያማረሩ ያሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
መሪዎች ራሳቸውን ከሕገ ወጥነት እና ከሌብነት እንዲያርቁም አሳስበዋል። ሌብነት አዋራጅ፣ ታሪክን የሚያበላሽ፣ ልጅን የሚያሳፍር እና ሀገር የሚያሳጣ ተግባር ነው ብለዋል።
ሌብነት እና ሕገ ወጥነት ሕዝብን የሚያማርር እና ግጭት የሚያባብስ መኾኑንም ተናግረዋል። ጽንፈኛውን ከጠላት የመነጠል፣ ሕዝቡ በጽንፈኛው ላይ እንዲነሳ፣ መደበቂያ፣ ስንቅ እና ትጥቅ አቀባይ እንዳይኾን ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። የሕዝብ ዋስትናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል መኾኑን ተናግረዋል።
የጸጥታ ኃይሉ በየአካባቢው ያለውን ጽንፈኛ እየተከታተለ እንዲያጸዳ ማድረግ እንደሚጠበቅም አመላክተዋል። የጠላትን አቅም እና የአቅም ምንጭ ማጥፋት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ለጠላት መረጃ የሚያቀብሉትን ማጽዳት እና መነጠል እንደሚያስፈልግም አንስተዋል። የፖለቲካ እና የሕዝብ ግንኙነት ሥራውን በተገቢው መንገድ እንዲሠሩም አስገንዝበዋል። ማስተዋል እና ብልሃት እንዲኖር ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
ሕዝብን እስከ ታች ድረስ በመውረድ ማወያየት እና መደገፍ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። “መሪዎች ለምትመሩት ታላቅ ሕዝብ የሚመጥን ታላቅ ሥራ ተግብሩ” ነው ያሉት።
ታላቁ ሕዝብ አንገቱን እንዳይደፋ፤ ቀዳሚ እንጂ ተከታይ እንዳይኾን ታሪካዊ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
ልጆቻችን የሚኮሩበትን ታሪክ፣ ልጆቻችን የሚመኩባትን ሀገር ለትውልድ ከነ ሙሉ ክብሯ ማስተላለፍ አለብን ነው ያሉት።

