“የጉባ ብስራቶች ፤የመደመር መንግስት ትሩፋቶች” በሚል መሪ ሀሳብ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ አመራሮች ከጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል እንደገለፁት የምንገነባው ስርዓት ከራሳችን ምንጭ የተቀዳ መሆን አለበት ብለዋል።
ጎንደር የጥበብ አፍቃሪ ፣የእንግዳ አክባሪ ምድር ናት ያሉት ሚኒስትሯ ጎንደር የሚመጥናትን ስፍራ ለመያዝ ዝግጅት ላይ መሆኗን መገንዘባቸውን ገልጸዋል ።
የምናደርገው የህዝብ ምክክር ለምንገነባው የዲሞክራሲ ስርዓት መሰረት መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሯ ባለፉት 8 ዓመታት በኢትዮጵያ በአራቱ ማዕዘናት የልማት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ተገቢውን ስፍራ ትዕዝ ዘንድ ዜጎች በተሰማሩበት ዘርፍ የራሳቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) የብልጽግና ጉዟችን የሚያመላክቱ በርካታ የልማት ስራዎች በከተማው እየተሰሩ ይገኛል ብለዋል።
ለውይይቱ ተሳታፊዎች እንኳን ደህና መጣችሁ መልክት ያስተላለፉት የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻለቸው ዳኘው የከተማችን የቀደመ ሥልጣኔ በዋናነት በመደመር መርህ የቆመ ነው ስንል ዘመኑን ለመምሰል የምንለው የሚመስለው ብዙ አለ።
ዘመኑ ጎንደርን እንደሚመስል በታሪክም በሚዳሰስ ማስረጃም ማሳየት እንችላለን ብለዋል።
የእምነትም፤ የማንነት ብዝኃነትም ተጋምዶና ተደምሮ ጎንደርን ሲሰራ ኖሯል።
በእያንዳንዱ የጎንደር የቀደመ የታሪክ አሻራ የአይሁድ፣ ክርስትናና እስልምና የተደመሩ አሻራዎች ያሉት መሆኑን ገልፀዋል።
በሌላ በኩል እንኳን የኢትዮጵያ የሌላ ዓለም ሰዎች ቀለምም በመዲናችን ስልጣኔ ላይ የተደመረ ድርሻ አላቸው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከፖርቱጋል እስከ የመን ከህንድ እስከ ቱርክ፣ ከጣሊያን እስከ እንግሊዝ ጎንደር የሀገርም የዓለምም ዜጋ አብሮነትና ድምር ገፅ የሰራት መሆኑን ተናግረዋል።
የጎንደር የአብሮነት መናገሻነት በጋራ ሰራናት የምንላት ብቻ ሳትሆን በጋራ የእኛ የምንላት ከተማ ፈጠረ።
እርግጥ ነው ጎንደር “የእናንተ ነኝ” በማለቷ ስለ መደመር፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት ዋጋ ስትከፍል ኖራለች ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በልማት እንድትጎተት፣ በስቃይ እንድትኖር ትኩረት እንድትነፈግ እና በፀጋዋ እንዳትለማ ተደርጋ መቆየቷን ተናግረዋል።
በትንሹ ለማየት እንደሞከራችሁት፣ ዛሬ በጎንደር እየሰራን ያለንው ትናንትናን ጭምር ነው፡፡
ያም ሆኖ ብዙ ስኬታማ ለውጦች አስመዝግበናል:: ስኬቶቹ የበለጠ እንድናልም እንጂ ተመራርቀን እንድንለያይ አላደረጉንም ብለዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር)፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያዊ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር)፣ የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ በሪሁን መንግስቴ እና የከተማው ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

