(ታሕሳስ 04/2018 ዓ.ም) የክልል እና የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ መሪዎች “የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች” በሚል መሪ መልዕክት በወቅታዊ ክልላዊ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ በደሴ ከተማ ከልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተዋል።
የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አወሉ አብዲ፣ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሀ ደሳለኝ፣ የከተማ አሥተዳደሩ እና የዞኑ መሪዎች በመድረኩ ተገኝተዋል።
የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት የበለጠ በመጨመር የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በተለይም የግብርና ሥራን በውጤታማነት በመተግበር ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል፤ ይህም የብዙ ኢትዮጵያውያንን ሕይዎት አሻሽሏል ነው ያሉት።
ብልጽግና ፓርቲ እሳቤው ከፍታ ነው፤ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን ይዞም እየሠራ ነው ብለዋል።
አንድ የሚያደርጉንን ጉዳዮች በማጠናከር፣ አንድነት እና ሰላማችንን የሚያናጉ ነገሮችን ደግሞ በመቅረፍ በከፍታ ላይ የቆመች ሀገር ለመገንባት እየተሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
እንልማ ማለት ተገቢ ጥያቄ ነው፣ የወሎ አካባቢ ሕዝብም ዛሬ ይህንኑ ጥያቄ ነው ያነሳው፤ መንግሥት ጥያቄውን ለመመለስ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
ተጀምረው ያልተቋጩ ልማቶች እንደሚጠናቀቁ እና አዳዲስ ልማቶችም እንደሚጀመሩ ተናግረዋል። ለዚህም በጋራ መሥራት እና የመንግሥትን አቅምም ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አወሉ አብዲ ወሎ ከጦሳ ተራራ የገዘፈ ፍቅር እና አንድነት የነገሠበት ነው ብለዋል።
ወደ አማራ ክልል ዘልቀው ከወሎ ሕዝብ ጋር መወያየታቸው እንዳስደሰታቸውም ጠቅሰዋል።
ሀገራችን ባለፉት ዓመታት ተስፋ የሚሰጡ ለውጦችን እና ሥጋቶችን ስታስተናግድ ቆይታለች፤ ለውጦችን ለመናድ እና ሀገርን ለውጭ ጠላት ለማጋለጥ የሚጥሩ አካላት የጠነሰሱትን ጦርነትም አስተናግደናል ነው ያሉት።
ይህም የታቀዱ የልማት ሥራዎች በሙሉ አቅም እንዳይከናወኑ እንቅፋት ኾኖ ቆይቷል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አሻጥሮች እና የብድር ክልከላዎችም ገጥመዋት ነበር ነው ያሉት።
በራስ አቅም በመቆም ወደ ልማት ተገብቶ በስንዴ ልማት ታሪክ ተሠርቷል፤ በሁሉም ግንባር ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ዘመቻም አሸንፈን ከችግር ሸለቆ ወጥተናል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በጸጋዋ መጠቀም እንጂ የሰው ሀገር ሀቆችን መንካት አትፈልግም ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጸጋን የመጠቀም ተግባራዊ ብስራት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ግድባችንን በመረቅንበት ዕለትም ታላላቅ የጉባ ብስራቶችን አልመን እየሠራን ነው ብለዋል።
የጉባ ብስራቶች ትውልድ ቀያሪ ፕሮጀክቶች ናቸው፤ እነዚህ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ የከፍታ ጉዞዋ ይረጋገጣል ነው ያሉት።
ሀገራችን ተዝቆ የማያልቅ ሃብት አላት፤ ይህንን በመጠቀምም ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት። ይህ እንዲኾን ደግሞ በራስ አቅም ቆሞ መሥራት ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያዊ አንድነት መንፈስ በመቆም እና አንዱ ለሌላው በመተሳሰብ በጋራ መሥራት ይገባልም ብለዋል።
የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ፣ አቅመ ደካማዎችን ለመደገፍ፣ የትምህርት ቤት ምገባን ለማስፋፋት፣ የሥራ እድል ለመፍጠር እና ሰው ተኮር የኾኑ ሥራዎችን ለማከናወን እንደ መንግሥት በትጋት እየተሠራ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ የከፍታ ጉዞ በአንድነት ቆሞ መሥራት ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል አቶ አወሉ።

