ታሕሳስ 4/2018 ዓ.ም)፦ በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ለምርት ስብሰባ የደረሰን ሰብል ከብክነት በፀዳ መልኩ እየተሰበሰበ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በዞኑ የሰብል አሰባሰብን በተመለከተ የዞኑን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ አበባው እንየው ለኢዜአ እንደገለጹት የመኸር ሰብል ስብሰባው የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም እየተከናወነ ይገኛል።
ባለሙያው በማብራሪያቸው የደረሰውን ሰብል ብክነትን በሚያስቀር መልኩ በወቅቱ የመሰብሰብ ተግባር መከናወኑን ገልጸዋል።
የሰብል አሰባሰቡ ኮምባይነርን ጨምሮ በደቦ፣ በልማት ቡድን አደረጃጀት እና ሌሎችም አማራጮች እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም በመኸር ወቅቱ በሰብል ከተሸፈነው 640 ሺህ ሄክታር እስካሁን ከ300 ሺህ በላይ በላይ የደረሰ ሰብል ተሰብስቧል ብለዋል።
የቀረውም ሰብል በቀጣይ ጥቂት ቀናት ተሰብስቦ የሚጠናቀቅ መሆኑን ገልጸው ከለማው ሰብልም ከ25 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት የሚገኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአነደድ ወረዳ የጃማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ምህረት በቃሉ እና በባሶሊበን ወረዳ የልምጭም ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ታደገ ልየው፤ በመኸር ያዘመሩትን የጤፍ፣ የስንዴ፣ የበቆሎ እና ገብስ መሰብሰባቸውን ገልጸዋል።
በመንግስት በተደረገላቸው እገዛ የምርት ብክነትን በሚያስቀር መልኩ ምርቱን መሰብሰባቸውን ተናግረዋል።
በአማራ ክልል በመኸሩ ከለማው 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል።

