“ሰላምን የሚያስጠብቀው ሕዝብ ነው” አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)

(ታኅሣሥ 03/2018 ዓ.ም) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምዕራብ ጎጃም ዞን ከደጋ ዳሞት ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል መላኩ ገላነህ ደጋ ዳሞት ተማሪዎችን፣ መምህራንን እና መሪዎችን በግፍ የጨፈጨፈ ታጠቂ ቡድን የሚንቀሳቅስበት መኾኑን ተናግረዋል።

በደጋ ዳሞት መሪዎች በግፍ ተጨፍጨዋል፤ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል ነው ያሉት።

ታጣቂው ቡድን ወደ ጫካ የወጣው ሥልጣንን በኀይል ለመያዝ ነው ያሉት አዛዡ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር የሚሠራ ነው ብለዋል። በየቀኑ ገንዘብ አምጡ የሚላችሁን፤ ልጆቻችሁን ከትምህርት ገበታ ውጭ ያደረገውን ማውገዝ እና መታገል ይገባችኋል ነው ያሉት።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ ረጋሳ ይህ ኩሩ ሕዝብ እና ሀብታም አካባቢ በሰላም እጦት መኖር አይገባውም ብለዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት በየአካባቢው እየተንከራተተ የሚገኘው ሰላምን ለማረጋገጥ እና ልማት እንዲመጣ መኾኑን ተናግረዋል።

ልጆች እንዲማሩ፣ ልማት እንዲፋጠን ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት። በታሪካችን ነጭን አናስገባም ብለን ነጻነታችንን ያስከበርን፤ ሀገራችንን በጠላት አናስረግጥም ያልን፤ ተሳስቶ ቢረግጥ እንኳን አፈር ይዞ እንዳይወጣ የእግሩን አፈር እንዲያራግፍ የምናደርግ ኾነን ሳለ ዛሬ እርስ በእርሳችን የምንገዳደል ኾናል ነው ያሉት።

ሀገርን በአንድነት ያስከበሩ የእነዚያ ጀግኖች አባቶች እና እናቶች ልጆች ኾነን ሳለ በእርስ በርስ ግጭት መኖር አይመጥነንም ብለዋል። ሐቀኛ በመኾን ለሰላም መወያየት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሰላምን ለማረጋገጥ የሰላም አማራጭ ተደጋጋሚ እየቀረበ ነው፤ የሰላም አማራጭን የሚቀበሉትን በፍቅር እንቀበላለን፤ የሰላም አማራጭን በማይቀበለው ግን እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል።

መለዮ ለብሰን ቃል የገባነው ለእናንተ ሰላም እና ክብር ነው፤ በሕዝብ ላይ ግፍ በሚፈጽሙት ላይ እርምጃ እንወስዳለን ነው ያሉት። የቆምነው ሀገር ብለን ነው፤ ሌላ ዓላማ እና ግብ የለንም ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በጫካ የወጡትን እንዲመክሩ ጠይቀዋል። ልጆች እንዲማሩ፣ ሽማግሌዎች እንዲጦሩ ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) አካባቢው ከከፋ ችግር ወጥቶ ወደ አንጻራዊ ሰላም መሸጋገሩን ተናግረዋል።

በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም እንዲፈጠር ላደረገው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ የጸጥታ ኀይል እና ሰላም ወዳዱ ሕዝብ ምስጋና ይገባል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ልማት እና እድገት የማይደሰቱ ታሪካዊ ጠላቶች አሉ ያሉት አስተባባሪው የኢትዮጵያ እድገት የሚያንገበግባቸው ጠላቶች የውስጥ ግጭትን እንደ መልካም አጋጣሚ ይጠቀሙበታል ብለዋል። የውጭ ጠላቶች በአማራ ክልል ያለው ግጭት እንዲቀጥል እንደሚፈልጉም ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ያለው ግጭት የጠላት ተልዕኮ መኾኑን መረዳት እና በአንድነት ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ሰላምን የሚያስጠብቀው ሕዝብ ነው፤ ሕዝብ በውስጡ ያለውን የሰላም ጸር እረፍ ካላለ ሰላም አይረጋገጥም፤ በየአካባቢው የጸጥታ ኀይል ተሰማርቶ ሰላምን አያረጋግጥም፤ ሰላምን የሚያረጋግጠው ራሱ ሕዝብ ነው ብለዋል።

እየገደላችሁ ያለውን ታጣቂ ቡድን ደፍራችሁ አውግዙ፤ ደፍራችሁ ካላወጋዛችሁ ሰላም አይመጣም፤ ልጆቻችሁ አይማሩም ነው ያሉት።

በደጋ ዳሞት ከፍተኛ የኾነ የትምህርት ስብራት መፈጠሩንም ተናግረዋል። ሰላም የሚፈልግ ሰላም የሚነሳውን ማውገዝ እንደሚገባው ገልጸዋል።

የተጠየቁ የልማት ሥራዎች እንዲመለሱ ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ከዚህ በላይ ግፍ መቀጠል የለብትም ነው ያሉት። የመንግሥት የሰላም በር ሁልጊዜም ክፍት መኾኑንም ተናግረዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top