(ታኅሣሥ 03/2018 ዓ.ም) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምዕራብ ጎጃም ዞን ከደጋ ዳሞት ወረዳ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።
በውይይቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት
ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ ደጋ ዳሞት የሊቃውንት እና አስታራቂ የሀገር ሽማግሌዎች መገኛ ነው ብለዋል።
የሊቃውንት ሀገር ደጋ ዳሞት ባለፉት ሁለት ዓመታት ሥልጣንን በኃይል ለመያዝ በተነሳው ጽንፈኛ ቡድን በደል ደርሶበታል፤ የጭካኔ ድርጊት ተፈጽሞበታል ነው ያሉት።
መሪዎች በግፍ የተገደሉበት፤ የሕዝብ እና የመንግሥት ንብረት የወደመበት መኾኑንም ተናግረዋል።
በደጋ ዳሞት የተፈጠረው በደል ተነግሮ የማያልቅ ብዙ ነው ብለዋል። የሊቃውንት መፍለቂያ የነበረው አካባቢ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲኾኑ አድርጓል ነው ያሉት።
ዳሞት ከዚህ በኋላ በቃህ ማለት አለበት፤ በጫካ የሚገኙትን ግቡ ማለት አለበት ነው ያሉት። ሰላሙን በዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚገባው ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ደጋ ዳሞት የግፍ ግፍ የተፈጸመበት፣ የግፍ ጽዋ የፈሰሰበት ነው ብለዋል። መሪዎች በአሰቃቂ በደል የተገደሉበት መኾኑንም ተናግረዋል።
“ከዚህ በላይ የግፍ ጽዋ እንዲፈስ መፍቀድ አይገባም” ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ በውይይት እና በምክክር ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ሰላምን ማረጋገጥ ካልተቻለ በደጋ ዳሞት መሪዎች ላይ የደረሰው ግፍ በእያንዳንዱ ሰው መድረሱ አይቀርም ብለዋል። ለዘላቃ ሰላም ሀቀኛ ውይይት እና እውነተኛ መፀፀት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

