“የጥበበኛ ሰው የመጀመሪያው መለያ ግፍን ማውገዝ ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

(ታኅሣሥ 03/2018 ዓ.ም) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምዕራብ ጎጃም ዞን ከደጋ ዳሞት ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ሰላም የሚረጋገጠው መንግሥት እና ሕዝብ ተቀናጅተው ሢሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።

አስታዋይ ሕዝብ የሚጠበቅበትን ያውቃል፤ ግዴታውንም በአግባቡ ይወጣል ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ነጻነትን ያለ ገደብ ለመጠቀም እየሻቱ ግዴታን አለመወጣት ለሀገር እና ለሕዝብ አይጠቅምም ብለዋል።

የጥበበኛ ሰው የመጀመሪያው መለያ ግፍን ማውገዝ ነው፤ ከደጋ ዳሞት የሚጠበቀውም እንዲ ነው፤ ባለፉት ዓመታት ግን ይሄን በማድረግ ክፍተት ታይቷል፣ ግፍን ማውገዝ ይጠበቅባችኋል፤ ሰላም የሚጀምረው ግፍን በጽኑ ከማውገዝ ነው ብለዋል።

በሃሰተኛ መረጃ መናድ እና ላልተገባ ድርጊት መነሳት እንደማይገባ ተናግረዋል።

ብልሃት ያለው ሕዝብ የአንድን ችግር መነሻ ምክንያት መርምሮ ያውቃል፤ አውቆ ይረጋጋል፤ መፍትሔም ይፈልጋል ነው ያሉት።

በግፍ የተገደሉት መሪዎች አገዳደል ካልቆጫችሁ፤ የንጹሐን ሞት ካላሳዘናችሁ ችግሩ ሊቆም አይችልም ብለዋል።

ሀገር እንዲጸና አንድነት፣ ወንድማማችነት እና አብሮነት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ሕዝብን በሀሰተኛ መረጃ እንደሚያወናብዱ ገልጸዋል። ሕዝቡ ከሀሰተኛ መረጃ እና ፕሮፓጋንዳ እንዲጠበቅም አሳስበዋል።

ሥልጣንን በኃይል ለመያዝ የተነሱ፣ ኢትዮጵያን ከባዕዳ ጋር በመላላክ ለማሳነስ የሚሠሩ አሉ ብለዋል።

ሀገርን ለማሳነስ የሚሠራን ቡድን ደግሞ መታገል እንደሚገባ አመላክተዋል።

መንግሥት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ማድረጉን ተናግረዋል።

በተደረገው ተከታታይ የሰላም ጥሪ በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን መቀበላቸውን ገልጸዋል።

በቅርቡ ደግሞ የዘላቂ ሰላም ስምምነት ማድረጋቸውን አንስተዋል።

ሰላምን ለማረጋገጥ እውነትን መያዝ፣ ለሐቅ መሥራት እና በጋራ መቆም ይገባል ነው ያሉት።

የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሰላምን መስበክ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

የአካባቢው መሪዎች ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ እንዲሠሩም አሳስበዋል። ውስጣዊ አንድነት እንዲጠናከር እንዲሠሩም አስገንዝበዋል።

ሕዝቡ ከሥነ ልቦና ጫና እንዲወጣ እና ለሰላም እንዲነሳ ማድረግ እንደሚገባም መክረዋል።

ልጆቻችንን ከትምህርት ገበታ አታስቀሩ ብላችሁ በአንድነት ከተነሳችሁ ጥፋትን ማስቆም እና ሰላምን ማረጋገጥ ትችላላችሁ ነው ያሉት።

ወደ ዘላቂ ሰላም ለመሸጋገር በአንድነት መሥራት እንደሚጠበቅም አመላክተዋል።

አጥፊዎችን ሲያወግዙ፣ ሲያጋልጡ እና ሰላምን ሲያረጋግጡ የልማት ሥራዎች እንደሚፋጠኑም ተናግረዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top