“በሕፃናት እና ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመቅረፍ ሁሉም በየድርሻው ርብርብ ሊያደርግ ይገባል” ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይ

(ታኅሣሥ 03/2018 ዓ.ም) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከፕላን ኢንተርናሽናል ጋር በመተባበር በጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ በተለይም የፆታ ተኮር ጥቃትን መከላከል እና ምላሽ መስጠት ዙሪያ ውይይት እያደረገ ነው።

የፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ኀላፊ ምስክር ገበየሁ (ዶ.ር) ሁሉም ሕፃናት እኩል እድል እንዳላቸው እና ይህንን እድል በመጠቀም ሕልማቸውን እንዲያሳኩ መደገፍ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ይህንን በመረዳትም ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ ሕፃናት ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው ለስኬት እንዲደርሱ ለማስቻል ላለፉት 51 ዓመታት ፕላን ኢንተርናሽናል በሁሉም ክልሎች እየሠራ ስለመኾኑ ተናግረዋል።

በዓለም ለ34ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ለ20ኛ ጊዜ የተከበረውን የፀረ ፆታዊ ጥቃት ንቅናቄ ፕላን ኢንተርናሽናል በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ማክበሩንም ተናግረዋል።

በቴክኖሎጂ የተደገፈ ፆታዊ ጥቃትን ማለትም የግለሰቦችን ምስል እና ቪዲዮ ተገቢ ባልኾነ መንገድ በማቀናበር ማሳደድ እና ለጥቃት በማመቻቸት የሴቶችን ደኅንነት አደጋ ውስጥ መጣል እየተለመደ መጥቷል ሲሉ ተናግረዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሦሥት ሴቶች አንዷ አካላዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት እንደሚደርስባት ጥናቶች ያሳያሉ ብለዋል።

በኢትዮጵያ ደግሞ 26 በመቶ የሚኾኑ ሴቶች አካላዊም ኾነ ወሲባዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል ነው ያሉት። ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከል በጋራ መረባረብ ይኖርብናል ብለዋል።

በሀገራችን በርካታ ጠቃሚ ባሕላዊ እሴቶች እና ልምዶች ባለቤቶች የኾነውን ያክል በሕዝባችን ብሎም በሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያሳድሩ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች የሚፈፀምባት ሀገርም ናት ያሉት የአማራ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ናቸው።

በዋናነት በክልሉ በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚፈፀሙ በርካታ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች እና ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች የሚፈፀምበት ክልል ነው ብለዋል።

እነዚህን ተፅእኖዎች ለመቀነስ ባለፉት ዓመታት በተሠሩ ሥራዎች የድርጊቱን ሥርጭት በተወሰነ መልኩ መቀነስ ተችሏል ነው ያሉት።

በቀጣይ የልጅነት ጋብቻ እና ሌሎች በሕፃናት እና ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን የሚያስከትሉትን ዘርፈ ብዙ ችግር በመገንዘብ በጋራ ለመቅረፍ የሚያስችል ሥራ ለመሥራት ሁሉም በየድርሻው ርብርብ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

በመድረኩ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ፋንቱ ተስፋየን ጨምሮ የተለያዩ የሥራ ኅላፊዎች ተገኝተዋል ሲል የዘገበው አሚኮ ነው።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top