(ታህሳስ 3/2018 ዓ.ም) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ የኃይል ሽግግር ታሪክ ቀያሪ አቅም መፍጠሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ።
ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር በማለም ለኬንያ፣ ጅቡቲና ታንዛንያ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ላይ ትገኛለች።
እስከ ህዳር 30 ቀን 2018 ዓም 15 ሺህ 313 ጊጋ ዋት ሰዓት ሃይል የተመረተ ሲሆን ባለፉት አራት ወራት 733 ጊጋ ዋት ሰዓት ለውጭ ሀገራት ቀርቧል።
ለጎረቤቶቿ የምታቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭም የቀጣናውን ሀገራት ዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማሻሻል ለኢትዮጵያም የውጭ ምንዛሬ ገቢ በማስገኘት ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማስፋት የተወሰዱ እርምጃዎች ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ ነው ብለዋል።
የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ጣቢያዎችን ኃይል የመሸከም አቅም በማሳደግ ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ ለውጭ ሀገራት የኃይል አቅርቦት ማሻሻል እየተቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም 5ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኃይል ወደማመንጨት መሸጋገሩም በኃይል አቅርቦት ፍላጎት ላይ ታሪክ ቀያሪ አቅም መፍጠሩን አስረድተዋል።
በዚህም ሕዳሴ ግድብ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከምታመርተው 9ሺህ 750 ሜጋ ዋት የኃይል አቅርቦት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን በመሸፈን የአንበሳውን ድርሻ እንደያዘ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የአቅም ሽግግርም የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት በማሳለጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩ አልሚዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፋላጎት ምላሽ በመስጠት በሙሉ አቅማቸው የሚያመርቱበት ሁኔታ መፈጠሩንም ገልጸዋል።
ሕዳሴ ግድብ የፈጠረው የኃይል አቅርቦት አቅም ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለኢኮኖሚ መነቃቃት ገንቢ ሚና ያላቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲፈጠሩ እያደረገ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኅይል ሀገር ውስጥ ከሚሰጠው አገልግሎት ባሻር ለሌሎች ሀገራት ኅይል በማቅረብ ለቀጣናዊ ትስስር የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሀገራት ጋር የተፈጠረው የኅይል ትስስር የጋራ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ መልካም ጉርብትና መፍጠር የሚያስችል ነው ብለዋል።
ይህም የአፍሪካ ህብረት የቀረፀው አጀንዳ 2063 አባል ሀገራቱን በመሰረተ ልማት የማስተሳሰር ግብ እንዲሳካ ኢትዮጵያ እየተንቀሳቀሰች እንደምትገኝ ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።

