ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሰፊ የሪፎርም ማዕቀፍ ነድፎ በመተግበር ላይ ነው። ይህም ሰባት ዋና ዋና አምዶች ያሉት ነው።
አምዶቹም፦
1. የኢንዱስትሪ፣ ሙያ ምድብ እና ክፍያና ጥቅማ ጥቅም ማሻሻል
2. የሙያ ብቃት ግንባታ፣
3. የአገልግሎት ማላቅ፣
4. ዘመናዊ የሰው ኃይል አመራር፣
5. የብዝሃነትና አካታችነት ማረጋገጥ፣
6. ዲጂታላይዜሽ ማስፋፋት እና፣
7. የአመራር አቅም መገንባት ናቸው።
እነዚህ ሥራዎችን ለማስተግበር ፈጻሚ እና ባለቤት ተቋማት በዌቮች (Wave I, Wave II & Wave III) ተከፋፍለው ወደ ትግበራ የተገባ ሲሆን አፈጻጸሙም ተስፋ ሰጪ ነው።
ከሰባቱ የሪፎርም አምዶች አንዱ የአገልግሎት አቅርቦት ሂደቱን ማላቅ ነው።
በተደረገው የአፈጻጸም እንቅስቃሴ ተጨባጭ እና በኢትዮጵያ የመንግስት አገልግሎት ማሻሻል ብቻ ሣይሆን ማላቅም እንደሚቻል በተግባር ታይቷል።
የፌዴራሉን ጨምሮ እሰከ እዚህ ወር ባለው ጊዜ 21 የመሶብ (MESOB:-Modern Ethiopia Services for Organized Benefits) ተገንብተው በሥራ ላይ ናቸው።
በየማዕከላቱ የሚሰጡ አገልግሎቶች ዲጂታላይዝድ የሆኑ አገልግሎቶች ብቻ ናቸው።
የICT እውቀት የሌላቸውን ዜጎች የሚታገዙበት ሥርዓት እንዲኖረው ተደርጎ የተነደፈም ነው።
በአሁኑ ሰዓት ይህንኑ ወደ ሁሉም የኢትዮጵያ ከተሞች ለማስፋፋት በመረባረብ ላይ እንገኛለን።
ይህንን ሥራ የሚመራ እና በአፍሪካ ተምሣሌታዊ ተግባር እና ቁመና ያለው አደረጃጀት እና ሥርዓት ለመፍጠርም ጥረት እየተደረገ ነው።
ከእነዚህ ተግባራት አንዱ የተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት ግንባታ ማካሄድ ነው።
የግንባታ የጨረታ ሰነድ በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሳይሆን በኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (EEC) ተዘጋጅቶ እና በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ጸድቆ በ egp.mofed.gov.et አለም አቀፍ ጨረታው ወጥቷል።
ለእዚህም ዲዛይን እና ግንባታ ግልጽ ጨረታ ውድድር የዓለም አቀፍ እና የኢትዮጵያ ተቋራጮች እየተሳተፉ ነው። በጨረታው ሂደት ማን እንደሚያሸንፍ የሚታወቅ ነገር የለም።
ተወዳዳሪዎቹ ለመገምገም ከኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (EEC)፣ ከከተማ ልማትና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር እና ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የተውጣጡ ባለሙያዎች ተደራጅቶ በሥራ ላይ ናቸው። አሸናፊው ከሂደቱ ይለያል ተብሎ ይጠበቃል።
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ሂደቱን የሚያደናቅፍ እና መሠረት የሌለው እና የተዛባ መረጃ በአንድ የማህበራዊ ሚዲያ ተሰራጭቷል።
ትክክለኛ መረጃው ከላይ የገለጸው ስለሆነ ለእራሱ ታዕማኒነት ሲል ማህበራዊ ሚዲያው የተዛባውን መረጃ እንዲስተካከል እመክራለሁ።
ዶ/ር መኩሪያ ኃይሌ
የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር

