(ታኅሣሥ 02/2018 ዓ.ም) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምዕራብ ጎጃም ዞን ከቋሪት ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ ረጋሳ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የቆመው ለሀገር እና ሕዝብ ሰላም መኾኑን ተናግረዋል። ሠራዊቱ የሀገር ኩራት እና መከታ መኾኑን ገልጸዋል።
በግጭት ውስጥ የሚጎዳው ሕዝብ መኾኑንም ገልጸዋል። የአማራ ክልል ከሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ሳያገገም ወደ ሌላ ግጭት መግባቱንም አንስተዋል። ግጭቱ ክልሉን እየጎዳ ስለኾነ በውይይት ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ለሕዝብ የሚጠቅመው ሰላምን በጋራ ማረጋገጥ እና ልማትን ማፋጠን ነው ብለዋል። በጫካ የሚገኘው ኀይል ለሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ክብር የማይሰጥ መኾኑንም ተናግረዋል። ግጭት ብቻውን ሰላም አያመጣም፤ ሰላምን የሚያመጣው መወያየት እና መመካከር ነው ብለዋል።
የሊቃውንት እና የብልሆች መፍለቂያ የኾነው አካባቢ ሰላሙን በብልሃት መፍታት እንደሚገባው ተናግረዋል።
እርስ በእርስ መግባባት እና መስማማት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል። ሰላም ካለ ጎጃም ሀገርን መቀለብ የሚችል አቅም እንዳለውም ተናግረዋል። እንደ ሀገር የጋራ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ መግባባት ይገባናል ነው ያሉት።
የውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያ ሰላም እንዳትኾን እንደሚሠሩም አንስተዋል። በኢትዮጵያ የሚገኙ ባንዳዎችን ደግሞ እንደመሣሪያ እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የቋሪት እና አካባቢው ሕዝብ ሰላሙን ለማረጋገጥ በኅብረት መሥራት እንደሚገባው ተናግረዋል።
የሰላምን አማራጭ በማስቀደም የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
መንግሥትን በኀይል ለመጣል የተነሳው ታጣቂ ቡድን ኢትዮጵያን ከባዕዳን ጋር በመኾን ለማዳከም እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ከባዕዳን ተልዕኮ እየተቀበለ ኢትዮጵያን በሃብቷ እንዳትጠቀም፣ ብሔራዊ ጥቅሟን እንዳታረጋግጥ የተላላኪነት ተግባር እንደሚፈጽም ገልጸዋል።
ሀገርን ለሚጠበቅው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተገቢውን ክብር መስጠት፣ አብሮ መሥራት እና ሰላምን ለማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
መንግሥት ባደረገው ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ በሺህዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን መቀበላቸውንም ገልጸዋል።
በቅርቡ በተደረገው ሰላማዊ ስምምነትም በርካታ ኀይሎች ገብተዋል፤ እየገቡም ነው፤ ሌሎች እንዲገቡም ሰላማዊ ውይይት ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ከሰላም ውይይት ባሻገር በተወሰደው የሕግ ማስከበር ሥራ ክልሉ ወደ አንጻራዊ ሰላም መሸጋገሩን ተናግረዋል።
ታጣቂው ቡድን የያዘው መንገድ ለሕዝብ እንደማይጠቅም መረዳት ይገባል ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ከያዙት መንገድ ወጥተው የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ መሥራት ይጠበቅባችኋል ነው ያሉት።
የአካባቢው መሪዎች ከሕዝብ ጋር በመኾን ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
ሚሊሻውን እና ሰላም አስከባሪውን በማጠናከር ሕግ ማስከበር ይገባል ነው ያሉት። የውስጥ አንድነትን ማጠናከር እና ልማትን ማረጋገጥ እንደሚገባም አመላክተዋል።
ለዘላቂ ሰላም መሥራት የነገ ልጆች ላይ መሠረት መጣል ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ እውነት ላይ በመቆም ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እንዲሠሩ አስገንዝበዋል።
ሕዝብ ያነሳቸውን የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ለመመለስ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
በሌሎች አካባቢዎች ተፈናቅለው የሚገኙ ወገኖችን ለመመለስ መንግሥት በትኩረት እየሠራ ነው፤ ነገር ግን ተፈናቃዮችን ለፖለቲካ ግብ የሚጠቀም እና እንዳይመለሱ የሚሠራ ኀይል እንዳለም ተናግረዋል።
ለወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራም በትኩረት እንደሚሠራበት ገልጸዋል።

