(ታሕሳስ 2/2018 ዓ.ም) ለባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር እና ለሰሜን ጎጃም ዞን መሪዎች ”በመደመር መንግሥት እይታ፤ የዘርፎች እምርታ” በሚል መሪ መልዕክት ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና ተጠናቅቋል።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የበላይ ዘለቀ ክፍለ ከተማ የማኅበራዊ ልማት ዘርፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ብርቱካን ሞላ የተሰጠው ሥልጠና በሀገር ደረጃ ወደኋላ የቀረንባቸውን ዘርፎች አውቀን ለማልማት የሚያስችል ነው ብለዋል።
የግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ የኢንዱስትሪ፣ የቱሪዝም እና የከተማ መሠረተ ልማት ዘርፎች ውጤት የሚገኝባቸው በመኾናቸው በዝርዝር መሠልጠናቸውን አንስተዋል።
ግብርናውን ከኋላ ቀርነት በማውጣት፤ ኢንዱስትሪውን በማዘመን፣ ቱሪዝምን እና መሠረተ ልማትን በማስፋፋት ተጠቃሚ በሚኮንበት መንገድ ውይይት አድርገናል ነው ያሉት።
እንደ መሪነቴ የሚጠበቅብኝ ምን እንደኾነ ተገንዝቤያለሁ፤ ሁላችንም የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል ሥንሠራ ሀገራዊ ልማት እና ለውጥ ይመጣል ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ጊዜው ታከለ ለክፍለ ከተማ እና ለወረዳ መሪዎች የተሰጠው ሥልጠና ወቅቱን ተረድቶ የሚመራ መሪ መፍጠር መኾኑን ገልጸዋል።
ሥልጠናው ማኅበረሰቡን የሚያዳምጥ እና ብልጽግናን የሚያረጋግጥ መሪ የመፍጠር ዓላማ አለው ነው ያሉት።
የብልጽግና መዳረሻ የኾኑትን ከተሞች በማልማት እና ችግር ፈቺ መሪ በመፍጠር ሕዝቡ ተጠቃሚ እንዲኾን በእውቀት የሚመራ መሪ ለመፍጠርም ነው ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ሁሴን በሥልጠናው የተተኮረባቸው ዘርፎች ብልጽግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ናቸው ብለዋል።
በሥልጠናው የተገኘነውን እውቀት እና አቅም ለሌላውም ማካፈል እንደሚገባም ገልጸዋል።
እየተሻሻለ የመጣውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ እየተረዳዱ የመሥራትን አስፈላጊነትም አንስተዋል።
የቁጭት እቅዶችን ፈጽሞ በማሳካት የመንግሥትን ቃል መጠበቅ እና ቅቡልነቱን ማሳደግ፤
የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን መመለስ እና የማይቻሉትን በምክንያት ማስረዳት፣
አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል የኅብረተሰቡን እርካታ ማሳደግ እና ወደ ሕዝቡ ቀርቦ በማዳመጥ ችግሩን መፍታት እና ቁርጥ ያለ ምላሽ መስጠት፣
ጠንካራ እና እውነተኛ ምርጫ በማካሄድ ዴሞክራሲን ማጎልበት እንደሚገባም ኅላፊው አብራርተዋል።
ልማትን እና መልካም አሥተዳደርን ለማስፈን በየደረጃው ለሚሰጠው ሥልጠና መዘጋጀት እንደሚገባም ነው አቶ ሞላ ያሳሰቡት።
የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን የመሪዎችን አቅም ለማሳደግ በተደራጀ መልኩ መፈጸሙን ገልጸዋል።
የብልጽግና ርዕይ እና ፕሮግራሞች ትውልድን እንደሚያሻግሩ ግልጽ በማድረግ የተቀራረበ ግንዛቤ ይፈጥራል ብለዋል።
መሪ የሚፈተነው በተግባር ጊዜ መኾኑን የጠቀሱት ዋና አሥተዳዳሪው በየደረጃው ያለው የሥራ ኀላፊ ለተቀራራቢ አፈጻጸም ትኩረት መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል።
በመሪዎች፣ በባለሙያ እና በሕዝብ ውስጥ ያለ ሌብነትን መታገል እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥን የማሻሻል አስፈላጊነትም አስምረውበታል።
“ስኬት የሚገኘው በማቀድ ብቻ ሳይኾን በመፈጸም ጭምር ነው”። ያቀድነውን ካልፈጸምን
ሥርዓታችን አደጋ ላይ ይወድቃል። ስለዚህ ከፍተኛ የኾነ ርብርብ ያስፈልጋል ነው ያሉት። መሪዎች ሥልጠናን እና አፈጻጸምን እንዲያነጻጽሩም አሳስበዋል።

