(ታሕሳስ 02/2018 ዓ.ም) በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) እና በክልሉ መንግሥት መካከል የተደረሰው ዘላቂ የሰላም ስምምነት በድርጅቱ ሙሉ እውቅና ያለው መኾኑን አፋህድ አስታውቋል።
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) የፖለቲካ ዘርፍ ምክትል ኀላፊ እና የወሎ ቤተ አማራ ጠቅላይ ዕዝ የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ እያሱ አበራ ድርጅቱ የክልሉን ሕዝብ ጥያቄ ለማስመለስ ወደ ትግል ብንገባም “ለሕዝባችን ያመጣነው ለውጥ ባለመኖሩ የሰላም አማራጭን ተጠቅመን ወደ ዘላቂ የሰላም ስምምነት መጥተናል” ብለዋል።
ትግሉ በተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎች ጣልቃገብነት አደረጃጀቱ መከፍፈሉን በመጥቀስም ክልሉን እና ሕዝቡን የረጅም ጊዜ የጦርነት ሜዳ አድርገው ለመጠቀም እየሠሩ መኾኑን ጠቁመዋል።
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) የጎጃም ጠቅላይ ግዛት ዕዝ የፋይናንስ ኀላፊ ከፋለ ዓለሙ ክልሉን ለሁለንተናዊ ቀውስ እየዳረገው የሚገኘውን ጦርነት ለማስቆም ብቸኛው መፍትሔ የሰላም አማራጭ በመኾኑ ችግሮችን በውይይት ወደመፋታት አማራጭ መጥተናል ብለዋል።
ድርጅቱ ከክልሉ መንግሥት ጋር ያደረገው ዘላቂ የሰላም ስምምነት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ፤ ገበሬዎች ወደ እርሻቸው ፊታቸውን እንዲያዞሩ የሚያስችል እና ለሕዝቡ የሰላም እፎይታን የሚሰጥ መኾኑን ተናግረዋል።
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) የጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ እና የወሎ ቤተ አማራ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ የሕዝብ አሥተዳደር እና ማኅበራዊ ጉዳይ ዘርፍ ኀላፊ ግርማ እጅጋየሁ ሰላምን እናመጣለታለን ብለን ወደ ትግል ለገባንለት ሕዝብ የሰላም እጦት ምንጭ በመኾን ከጉዳት ውጭ ያተረፍንለት ነገር ባለመኖሩ የሰላም አማራጩን ተቀብለን እንደድርጅት ወደ ድርድር መጥተናል ነው ያሉት።
ከሰላም አማራጭ ውጭ የሚደረግ የትኛውም የትጥቅ ትግል ድርጅቱን የማይወክል መኾኑንም ገልጸዋል።
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) ሀገር አፍራሽ ከኾኑ እና ለግል ጥቅማቸው ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር ድርጅቱ ምንም ዓይነት ኅብረት የሌለው መኾኑን በመግለጽም ከውጭ ኃይሎች ተልዕኮ ተቀብለው የውክልና ጦርነት የሚያደርጉ አካላት ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጡም ጥሪ አቅርበዋል።

