(ታኅሣሥ 2/2018 ዓ.ም ) የአማራ ክልል ስቴት ዩኒቨርሲቲ አዲስ የተቋቋመበትን አዋጅ እና ደንብ ለማስተዋወቅ የፖናል ውይይት እያካሄደ ነው።
ከዚህ ቀደም የአማራ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት የነበረው በክልሉ ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 300/2017 የክልሉ አሥፈጻሚ ተቋም ኾኖ እንዲደራጅ መወሰኑን ተከትሎ የአማራ ክልል ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 266/2018 መሠረት የአማራ ክልል ስቴት ዩኒቨርሲቲ ኾኖ ተቋቁሟል።
የአማራ ክልል ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ማተብ ታፈረ (ዶ.ር) ውይይቱ የተዘጋጀው የተቋሙ ሠራተኞች በደንቡ ላይ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል ነው ብለዋል።
ደንቡ የተቋሙ ማቋቋሚያ ብቻ ሳይኾን አጠቃላይ አሠራሩን የሚወስን ገዥ መመሪያ በመኾኑ ሠራተኛው ሊያውቀው ይገባል ነው ያሉት።
“መሪ ማለት ለሚሠራበት ተቋም ራሱን የሰጠ” ባወቀው ልክ የሚችለውን ለማበርከት የሚታትር ሁሉ ነው ብለዋል።
መሪነት ባለ ነገር ላይ ሳይቆም በመጠየቅ፣ በመፈለግ እና አዲስ ሀሳብ በማመንጨት ነገሮችን መለወጥ ላይ እንደሚያተኩርም ተናግረዋል። ስለዚህ ሁሉም የተቋሙ ሠራተኞች መሪ ሊኾኑ ይገባል ነው ያሉት።
ተቋሙ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲያድግ በርካታ ተልዕኮዎች አሉት ያሉት ፕሬዝዳንቱ ተልዕኮዎቹን በአግባቡ ለመፈጸም የተቋሙን የሥራ ባሕል መቀየር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ለዚህም ሰዓትን አክብሮ በመሥራት፣ የተቋሙን ጥቅም በማስቀደም እና በግልጽነት ተከባብሮ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
አዳዲስ ሀሳብ ማፍለቅ ላይ ማተኮር፣ ከማፍለቅ ባለፈ መጀመር እና ማስቀጠል እንዲሁም ማሥፈጸም እንደሚገባም ነው የገለጹት።
ፕሬዝዳንቱ በአዲስ አስተሳሰብ እና አሠራር ሥራ ለመጀመር መዘጋጀት እንዳለባቸው ለተቋሙ ሠራተኞች መልዕክት አስተላልፈዋል ሲል የዘገበው አሚኮ ነው።

