የጎንደር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታ ከ72 በመቶ በላይ ደርሷል።

ታሕሳስ 2/2018 ዓ.ም) መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸውን አሠራሮች በማሻሻል፣ የዲጂታል ፈጠራዎችን በመጠቀም እና ባለሙያዎችን በማብቃት፣ ኢንቨስትመንትን ሲያጓትቱ እና የኢኮኖሚ እድገትን ሲያደናቅፉ የነበሩ አሠራሮችን ለማሻሻል የሚያስችል ሂደት ነው።

አገልግሎቱ ብልሹ አሠራሮችን በማስቀረት፣ ተገቢ አገልግሎት ለመስጠት እና ምቹ ኹኔታ በመፍጠር ለሀገራችን የኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ወደ ተግባር ተገብቷል።

በጎንደር ከተማ በወርሐ ነሐሴ 2017 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የግንባታ ደረጃው ከ72 በመቶ በላይ መድረሱን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ አስታውቋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ነጻነት መንግሥቴ በጎንደር ከተማ ግንባታው የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ሲገባ የዜጎችን እንግልት በመቀነስ ቀልጣፋ፣ ዘመናዊ እና ከብልሹ አሠራር የጸዳ አገልግሎት ተደራሽ እንዲኾን የሚያደርግ መኾኑንም ገልጸዋል።

አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ ከሰው ንክኪ ውጭ ኾኖ ዘመናዊ አሠራርን የተከተለ መኾኑ ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም እና ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚያግዝ ያነሱት ኀላፊው ይህም ሕዝብ የሚማረርበትን ብልሹ አሠራር እንደሚያስቀር አመላክተዋል።

በጎንደር ከተማ እየተገነባ ያለው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታ ሲጠናቀቅ ዘጠኝ የከተማ አሥተዳደሩ ተቋማት እና 54 አገልግሎቶችን እንደሚይዝ ተገልጿል። ለአገልግሎቱ መተግበሪያዎች እየበለጸጉ መኾኑም ተጠቅሷል።

አገልግሎቶችን ዲጅታላይዝ ከማድረግ ሥራ ጎን ለጎን ለሰው ኃይል ሥልጠና ለመስጠት በዝግጅት ላይ መኾናቸውንም አንስተዋል።

አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በተለያየ ቦታ መኾናቸው ተገልጋዮችን የሚያንገላታ ነው ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ ነዋሪው መቶ አለቃ መሠረት መኩሪያ ናቸው።

ካንዱ ተቋም ወደ ሌላኛው ተቋም በመንቀሳቀስ ሂደት መጉላላት እንዳለም ጠቁመዋል።

የተበታተነ አሠራር አድካሚ መኾኑን የሚናገሩት ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ሐረገወይን ልሳነወርቅ እስካሁን ያለው የአገልግሎት ኹኔታ የተገልጋዩን ጊዜ እና ገንዘብን የሚያባክን ነውም ብለዋል።

የተጀመረው የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ ሲጀምር ጊዜ እና እንግልትን የሚቀንስ እንደሚኾን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

በጎንደር ከተማ እየተገነባ ያለውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እስከ ታኅሣሥ 30/2018 ዓ.ም ድረስ በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መኾኑን ከአሚኮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top