ተቋርጦ የነበረው መደበኛ የመምህራን የስራ ቦታ ዝውውር ሊሠራ መሆኑ ተገለፀ።
ባለፉት ዓመታት በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ተቋርጦ የቆየው የመምህራን እና ትምህርት ቤት አመራሮች ዝውውር በዚህ ዓመት ሊሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደምስ እንድሪስ አስታውቀዋል።
ባለፉት ዓመታት በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር የመምህራን እና ትምህርት ቤት አመራሮች ዝውውር ለመሰራት ባለመቻሉ ምክንያት የስራ ቦታ ዝውውር የማግኘት እድል አጥተው የቆዩ መምህራን ለከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር ተጋልጠው ቆይተዋል።
በዚህ ዓመት ይህን የመምህራን እና የትምህርት ቤት አመራሮችን ችግር ሊፈታ የሚችል የዝውውር መመሪያ መሻሻሉን አቶ ደምስ ገልጸዋል።
መመሪያውን ለማሻሻል ያስፈለገበትም ምክንያት ከአቅም በላይ በሆኑ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት በነባሩ የዝውውር መመሪያ ሊፈፀሙ የማይችሉ ድንጋጌዎች በመኖራቸው እነዚህን ድንጋጌዎች በመለየት መመሪያውን ከወቅቱ ጋር ተጣጥሞ እንዲፈፀም በማስፈለጉ ነው።
አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ተግባራዊ በመደረጉ ምክንያት የታጠፉ የትምህርት ዓይነቶች በመኖራቸው እና የታጠፉትን የትምህርት ዓይነቶች ሲያስተምሩ የነበሩ መምህራን አዲስ በተመደቡበት የትምህርት ዓይነት ዝውውራቸው እንዲፈፀም ለማድረግ መሆኑ ተገልጿል።
የዝውውር ስርዓቱን ቀልጣፋ በማድረግ መምህራን እና የትምህርት ቤት አመራሮች በተመደቡበት ቦታ ተረጋግተው የተጣለባቸውን ትውልድ የመገንባት ሃላፊነት በአግባቡ እንድወጡ ለማስቻል ታስቢ ያደረገ ነው።
ፍትሃዊና ግልፅ የሆነ የስራ ቦታ ዝውውር በማከናወን የመርሱን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት ታሳቢ ያደረገ ነው።
አሳታፊና ተጠያቂነት ያለበት ዝውውር በማከናወን በዘርፉ የሚታየውን የሠው ሃይል ስምሪት ምጥጥኑን በማረጋገጥ የተማሪዎችን ውጤታማነት ለማሳደግ አስፈላጊ በመሆኑ ነው።
ታታሪና ብቃት ያላቸው መምህራን ወደ መምህርነት ሙያ በማምጣት በሙያው እንዲቆዩ ለማድረግ አስፈላጊነቱ ስለታመነበት የዝውውር መመሪያውን መሻሻሉን አቶ ደምስ አመላክተዋል።
ዝውውሩ ከመሠራቱ በፊት በተሻሻለው መመሪያ ላይ በክልሉ ለዘርፉ ባለሞያዎች ስልጠና ይሰጣል ብለዋል።
በየደረጃው ለሚገኙ ባለሙያዎች ፣ መምህራን እና የትምህርት ቤት አመራሮች ግንዛቤ ከተፈጠረ በኋላ መምህራን፣ ርዕሰ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች ከታህሳስ 30 እስከ ጥር 10 /2018 ድረስ ባሉት ቀናት የዝውውር ፎርም እንደሚሞሉ ተገልጿል።
መረጃዎቹ በየደረጃው ከተጠናቀሩና ከተረጋገጡ በኋላ የዓመቱ ማጠቃለያ ላይ ከክልል ጀምሮ እስከ ትምህርትቤት ድረስ ዝውውሩ እንደሚሠራ ኃላፊው ገልፀዋል።
ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ቢሮው የመምህራንን ዝውውር ወደ ድጅታል ለመቀየር ሶፍት ዌር እያለማ መሆኑን ከትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

