የአማራ ክልል መሪዎች እና የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ወረዳ “ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት ማኅበረሰብ አቀፍ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) ባለፉት ሁለት ዓመታት የክልሉ መንግሥት ያላሰለሰ የሰላም ጥሪ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።
በዚህም የሰላም አማራጭን ለተከተሉ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እና ትብብር ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል።
መንግሥት የማኅበረሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ድጋፍ እያደረገ እና በቁርጠኝነት እየሠራ ነው ያሉት ኀላፊው ማኅበረሰቡም ድጋፉን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዥ ጄነራል መለስ መንግሥቴ ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ ማኅበረሰባዊ አጋርነትን ማጠናከር እና ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
መከላከያ ሠራዊት ትልቅ ታሪክ ያለው ሀገራዊ ተቋም በመኾኑ ይሄን በመረዳት ማኅበረሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍ እና አጋርነት ማሳየት አለበት ብለዋል።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ ማኅበረሰቡ መደራጀት እና ሰላም ጠል ግጭት ፈጣሪ የኾኑ ኀይሎችን መታገል ይገባል ብለዋል።
በጸጥታ ችግር ምክንያት ማኅበራዊ አገልግሎቶች በመቋረጣቸው ማኅበረሰቡ ለችግር መጋለጡን ገልጸው ችግሮችን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
ታጥቀው በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን በመከተል እየገቡ ነው ብለዋል።
ስለኾነም በየአካባቢው የተጀመሩ የሰላም አማራጮችን በማስፋት ዘላቂ ሰላምን ማጽናት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ የሰላም ጥያቄ በጸጥታ ኀይሉ ጥረት ብቻ ሊፈታ አይችልም ብለዋል። ማኅበረሰቡም አጋርነቱን ማሳየት አለበት ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በበኩላቸው ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት ጥረት እያደረጉ መኾኑን ተናግረዋል።
የወረዳው ማኅበረሰብ ለሰላም ዘብ በመቆም የጸጥታ ችግር በሚፈጥሩ አካላት ላይ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከክልሉ የጸጥታ ኀይሎች ጋር በመቀናጀት ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መኾኑን ገልጸዋል።
የአካባቢውን ማኅበረሰብ የኑሮ ሁኔታ በዘላቂነት ለማሻሻል የሚያስችሉ የመሰረተ ልማት ሥራዎች እንዲሟሉም ጠይቀዋል።

