የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

(ታኅሣሥ 01/2018 ዓ.ም) የክልል እና የመከላከያ ሠራዊት የሥራ ኀላፊዎች በሰሜን ጎንደር ዞን የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ጎብኝተዋል።

በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) በከልሉ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለጓብኝዎች ምቹ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናዎኑ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት የቱሪዝም ፍሰቱ ተቀዛቅዞ መቆየቱን ነው የተናገሩት።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ተግባራትን በመከወን ፍሰቱን ወደነበረበት ለመመለስ እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።

በሀገራችን ከሚገኙ ፓርኮች መካከል በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ፓርኮች መካከል የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ አንዱ ነው ያሉት ዶክተር ዘሪሁን የፓርኩን የቱሪዝም ፍሰት ለማሳደግ ጥረት ሲደረግ መቆየቱንም አንስተዋል።

በዚህም የአካባቢውን ሰላም በማረጋገጥ ጎብኝዎች በነጻነት መጥተው መጎብኘት እንዲችሉ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር መቻሉንም ነው የገለጹት።

ፓርኩ ከጎንደር ከተማ በአንጻራዊነት በቅርብ ርቀት የሚገኝ በመኾኑ ለጎብኝዎች ምቹ መኾኑንም ነው የተናገሩት።

በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት እና ለጎብኝዎች ምቹ ኹኔታን በመፍጠር የገቢ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባም አብራርተዋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሥራ ኀላፊ ጄኔራል መለስ መንግሥቴ ሰላምን በማጽናት እና የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ምጣኔ ሃብታዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው ያሉት ጄኔራሉ በቀጣይም ዘላቂ ሰላምን በማጽናት ፓርኩን ከጥቃት መከላከል እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ ስሜን ተራራዎች ፓርክ የብርቅዬ እንስሳት እና የአስደናቂ መልክዓ ምድራዊ ገጽታ መገኛ የኾነ ድንቅ ቦታ ነው ብለዋል።

ፓርኩን በሚፈለገው ልክ ለዓለም ማስተዋወቅ እና የቱሪዝም መዳረሻነቱን ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት።

መንግሥት ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ የቱሪስት መዳረሻ የሆኑ ቦታዎችን የቱሪዝም ፍሰት ለማሳደግ እየሠራ እንደሆነም ገልጸዋል።

በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ቦታዎችን በማረጋጋት እና የጸጥታ ችግሮችን በመቅረፍ ለጎብኝዎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ጥረት ሲደረግ መቆየቱንም ተናግረዋል ሲል የዘገበው አሚኮ ነው።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top