(ታኅሣሥ 01/2018 ዓ.ም) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምዕራብ ጎጃም ዞን ከደምበጫ ከተማ አሥተዳደር እና ከደምበጫ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳን እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ የምንወያየው የጋራ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ነው ብለዋል።
ሰላም እየነሳ ያለው በጫካ የወጣው ኃይል ነው፤ ይሄን በግልጽ ማውገዝ ያስፈልጋል ብለዋል።
ለሕዝብ እታገላለሁ ብሎ የወጣው ጽንፈኛው ኃይል ሕዝብን እያሰቃየ መኾኑንም ተናግረዋል። በዘረፋ እና በውንብድና የተሰማራ ኃይል መኾኑንም ገልጸዋል።
ችግሮችን በውይይት መፍታት ይገባል፤ መካሪ ሽማግሌ፤ አስታራቂ የሃይማኖት አባት እያለ ችግርን በግጭት ለመፍታት መሞከር አግባብ አይደለም ነው ያሉት። እውነቱን መሠረት በማድረግ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ጽንፈኛው ቡድን ደሀ ገበሬዎችን የሚያሰቃይ፣ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ የሚያስቀር፣ ትምህርት ቤቶችን ካምፕ የሚያደርግ እና የሃይማኖት ተቋማትን እንደ ምሽግ የሚጠቀም ነው ብለዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እውነተኛ መረጃ ላይ መመስረት፣ ስለ እውነት መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚዋደቀው ለሀገር ሰላም እና ክብር መኾኑንም ገልጸዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ስለ እውነት እየመከሩ እና እየዘከሩ ሰላምን እንዲያረጋግጡም ጠይቀዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሰላምን ማረጋገጥ የሚያስችል ጸጋ እና አቅም እንዳላቸውም ተናግረዋል።
ሕዝብን አንገት እያስደፉ፣ እያሰቃዩ እና እየዘረፉ መኖር አይቻልም ነው ያሉት። ለሰላም በአንድነት ሥሩ፣ ከአቅማችሁ በላይ ሲኾን ደግሞ እኛ አለን እናግዛችኋለን ነው ያሉት።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ እድገት የማይዋጥላቸው ታሪካዊ ጠላቶች አሉ፤ እነዚህ ታሪካዊ ጠላቶች ደግሞ ኢትዮጵያ በግጭት ውስጥ እንድትቆይ ይሠራሉ ነው ያሉት። ይህን በመረዳት ለጋራ ሰላም በጋራ መቆም ይገባል ብለዋል።
በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ንጹሐን ተገድለዋል፤ ሃብት ወድሟል፤ የልማት ሥራዎች ተደናቅፈዋል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል ነው ያሉት።
በትምህርት ላይ የደረሰው ጉዳት ነገ የሚፈጥረው ስብራት ከፍተኛ ነው ብለዋል።
መንግሥት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ቅድሚያ ሰጥቷል፤ በሰጠው አማራጭም በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለዋል ነው ያሉት። በዓለም ታሪክ የግጭት መቋጫው ውይይት መኾኑንም ተናግረዋል።
ግጭቱ እንዲራዘም የሚፈልገው በግጭት የሚያተርፍ ብቻ ነው፤ በግጭት የተጎዳው ሕዝብ ግን ሰላምን ይፈልጋል ብለዋል። መንግሥት ሰላም እንዲረጋገጥ፤ ልማት እንዲፋጠን ይሠራል ነው ያሉት።
ለአማራ ሕዝብ እታገላለሁ የሚለው ጽንፈኛ ቡድን የአማራ ልጆች እንዳይማሩ፣ መምህራን እንዳያስተምሩ፣ የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች እንዳይፈቱ የሚያዘገይ ነው ብለዋል።
በየአካባቢው የተሰገሰገውን ጽንፈኛ ቡድን እያጋለጡ ማውጣት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። ሰላምን ከመንግሥት ብቻ መጠበቅ እንደማይገባም አመላክተዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለሀገር ክብር እና ሰላም የሚሠራ የሀገር ኩራት ነው፤ ለሠራዊቱ ተገቢውን ክብር መስጠት እና በዘላቂነት ሰላምን ለማረጋገጥ ከሠራዊቱ ጋር በጋራ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
የልማት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሠራም ተናግረዋል።

