ሰላም ሁሉንም ተጠቃሚ እና ትርፋማ ታደርጋለች።

(ታኅሣሥ 01/2018 ዓ.ም) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምዕራብ ጎጃም ዞን ከደምበጫ ከተማ አሥተዳደር እና ከደምበጫ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ ረጋሳን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በክልሉ ግጭት የተፈጠረው ሁላችንም የሚጠበቅብንን ባለመወጣታችን ነው ብለዋል።

የተፈጠረው የጸጥታ ችግርም ሕዝብን ለከፋ ጉዳት አድርሷል ነው ያሉት። ችግሮች በግጭት አይፈቱም ያሉት ነዋሪዎቹ የሰላም አማራጭን ማስቀደም ይገባል ብለዋል።

እየተደረገ ያለው የሰላም ጥሪ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፤ ታጣቂዎችም ለሕዝብ እና ለኢትዮጵያ ሲሉ እጃቸውን ለሰላም መዘርጋት አለባቸው ነው ያሉት።

ሕዝብ እሳት ላይ እንዳለ መረዳት ይገባል፤ እሳቱ ደግሞ ሁሉንም የሚበላ ነው ብለዋል። የጸጥታ ችግሩ ሁሉንም ተጎጅ የሚያደርግ እና ለከፋ ኪሳራ የሚዳርግ መኾኑንም ገልጸዋል። የውስጥ ግጭት ሀገር ያሳጣል እንጂ ሌላ የሚሰጠው ጥቅም የለም ነው ያሉት።

በግጭቱ የማይተካው የሰው ሕይዎት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፤ ልማት ቆሟል፤ ባለሃብቶች ተሰድደዋል፤ ከፍተኛ የኾነ ማኅበራዊ ቀውስ ደርሷል ብለዋል።

የዜጎች በሕይዎት የመኖር መብት ተጥሶ መቆየቱንም ገልጸዋል። ሕዝቡ ከጸጥታ ኀይሉ ጋር በመተባበር ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባውም ተናግረዋል።

እያንዳንዳችን የጎደለውን በመረዳት ለመፍትሔው መሥራት ይጠበቅብናል፤ ፍቅር፣ መተማመን እና አንድነት ዘላቂ ሰላምን ያመጣል ነው ያሉት።

የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ከልብ መምከር እና መዝከር እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ደምበጫ እና አካባቢው መካሪ እና አስታራቂ ሽማግሌዎች ያሉበት መኾኑንም አንስተዋል። ሰላም ሁሉንም ተጠቃሚ እና ትርፋማ የሚያደርግ መኾኑን ገልጸዋል።

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር፤ የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር እና ሌሎች ግጭት የሚያባብሱ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ አመላክተዋል። ሕዝብን እያማረሩ ሌብነትን እና ብልሹ አሠራርን ማስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል።

የደምበጫ ከተማ የመብራት፣ የውኃ እና ሌሎች ችግሮች እንዲፈታም ጠይቀዋል። የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች እንዲፈቱ ሰላምን በአንድነት ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ ደምበጫ እና አካባቢው የታላላቅ ሊቃውንት፣ የሀገር ሽማግሌዎች መገኛ መኾኑን ተናግረዋል።

ታላላቆቹ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለዘላቂ ሰላም መሥራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

ከችግር መውጣት የሚቻለው ችግሩ እየጎዳን መኾኑን በተገቢው በመረዳት እና ለመፍትሔው በጋራ መቆም ስንችል ነው ብለዋል። ለሰላም በጋራ መቆም ካልተቻለ ሰላምን ማረጋገጥ አይቻልም ነው ያሉት።

በአካባቢው በርካታ ተማሪዎች አሁንም ከትምህርት ገበታ ውጭ ናቸው ያሉት አሥተዳዳሪው ተማሪዎችን መያዣ ማድረግ አያስፈልግም፤ ይህ የትውልድ ጉዳይ ነው፤ ተማሪዎች እንዲማሩ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የመንገድ እና ሌሎች የልማት ሥራዎች የሚሠሩት ሰላም ሲኖር ነው፤ ያለ ሰላም የሚረጋገጥ ልማት የለም ነው ያሉት።

ለሰላም እውነትን መሠረት በማድረግ መወያየት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በሕዝብ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ተጠቅመው ለሰላም እንዲሠሩም ጠይቀዋል።

ለሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ከቆመው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል ጋር መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

መንግሥት በዞኑ ለልማት ጥያቄዎች ትኩረት ሰጥቷል ያሉት አሥተዳዳሪው በዞኑ ሰባት የአስፋልት መንገድ ፕሮጄክቶች እና የመብራት ሰብስቴሽን ግንባታ እየተካሄደ መኾኑን ተናግረዋል።

የተጀመሩት የልማት ሥራዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም አንስተዋል።

ሁላችንም ኀላፊነታችንን መወጣት ከቻልን ሰላምን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ እንችላለን ብለዋል ሲል የዘገባው አሚኮ ነው።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ለማግኘት ቀጣዮቹን ሊንኮች ይጫኑ።

Facebook https://www.facebook.com/share/1ZfJoPFYV7/

Ticktock https://www.tiktok.com/@amhara.region.pre?_r=1…

Telegram https://t.me/ANRS_PresidentOffice

Twitter https://x.com/AmGovernoffice/header_photo

You Tube https://www.youtube.com/@amhararegionpresidentoffic1192

WhatsApp https://whatsapp.com/channel/0029Vb6ZZXk1t90V1p2qyV03

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top