በ82 ሚሊዮን ብር በጀት የሚሠራ የትምህርት ቤት ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ።

(ታሕሳስ 01/2018 ዓ.ም) በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የማኅበረሰቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄ የሚመልስ እና በ82 ሚሊዮን ብር በጀት የሚከናወን የትምህርት ቤት ግንባታ ለማከናወን የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።

በደብረ ብርሃን ከተማ ጠባሴ ክፍለ ከተማ የምስረታ ቀበሌ ነዋሪዎች ደረጃውን የጠበቀ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ልጆቻቸውን ለማስተማር ሲቸገሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ልጆቻቸውን ለማስተማር ወደ ከተማ መላክ ይጠበቅባቸው እንደነበረ የተናገሩት ነዋሪዎቹ ላልተገባ የትራንስፖርት ወጭ ከመዳረጋቸውም በላይ ሕጻናቱ ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ኾነው እንደቆዩም ተናግረዋል።

የማኅበረሰቡን ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የገንዘብ ድጋፍ በቀበሌው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ለማከናወን የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።

የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሽት ቀበሌው በርካታ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ አርሶ አደሮች እና ተፈናቃዮች የሚኖሩበት እንደኾነ ተናግረዋል።

በማኅበር የተደራጁ ነዋሪዎች የሚገኙበት እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚገኝበት፤ እየሰፋ ያለ ቀበሌ ነው ብለዋል።

ኅብረተሰቡ ሲያነሳው የነበረው ተገቢነት ያለው ጥያቄ በመኾኑ ግንባታው በአጭር ጊዜ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ መቅደስ ብዙነህ የቀበሌው ሕጻናት ምቹ ባልኾነ የመማሪያ ክፍል በሳተላይት ትምህርት ቤት ሲማሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ትምህርት ቤቱን ወደ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማደጉንም ተናግረዋል፡፡

ዛሬ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት ግንባታ ሁለት የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ቤተ ሙከራ፣ የአሥተዳደር ክፍሎች እና መጸዳጃ ቤቶችን ያካተተ እና ደረጃውን ይኾናል ነው ያሉት።

የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ልማታዊ ሴፍትነት ፕሮጀክትን ወክለው በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ይሄነው መንግሥቴ ፕሮጀክቱ በ82 ሚሊዮን ብር በጀት የሚከናወን ሲኾን ግንባታው በስድስት ወር ጊዜ ሙሉ በሙሉ የሚጠናቀቅ መኾኑንም ነው የተናገሩት፡፡

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በክልሉ በርካታ የተቋማት ግንባታ ሥራዎችን እየተገበረ ይገኛልና ሊመሰገን ይገባል ብለዋል።

የትምህርት ቤቱ ግንባታ በተቀመጠለት ጊዜ እና በጥራት ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ ከተማ አሥተዳደሩ እና ማኅበረሠቡ የበኩላቸዉን ድጋፍ እና ክትትል እንዲያደርጉም አሳስበዋል ሲል የዘገበው አሚኮ ነው።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ለማግኘት ቀጣዮቹን ሊንኮች ይጫኑ።

Facebook https://www.facebook.com/share/1ZfJoPFYV7/

Ticktock https://www.tiktok.com/@amhara.region.pre?_r=1…

Telegram https://t.me/ANRS_PresidentOffice

Twitter https://x.com/AmGovernoffice/header_photo

You Tube https://www.youtube.com/@amhararegionpresidentoffic1192

WhatsApp https://whatsapp.com/channel/0029Vb6ZZXk1t90V1p2qyV03

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top