ትውልድን በሥነ ምግባር መገንባትና ተቋምን በግልጽ አሠራር መምራት ሙስናን የመከላከል ቁልፍ ተግባሮቻችን ናቸው።
ዛሬ በ22ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን የበዓል ማጠቃለያ መድረክ ላይ ተገኝተናል።
ሙስናን እንደ ብሔራዊ አጀንዳ እና ለብልጽግናችን ቀይ መሥመር አድርገን በመውሰድ በጸና አቋም ትግላችንን አጠናክረን ቀጥለናል።
መንግሥት የፀረ ሙስና ትግሉን ውጤታማ ለማድረግ በወሰዳቸው የሪፎርም ርምጃዎች ሀገርን ሊያፈርስ የደረሰውን ተቋማዊ ሙስና አስቀርቷል።
በሙስና የተመዘበረ ሀብትን የሚያስመልስ ዐዋጅንም አጽድቋል። በፍትሕ ተቋማቱ ላይም ሰፊ ሪፎርምን እያካሄደ ነው።
የመንግሥት አገልግሎትን ግልጽና ቀልጣፋ ለማድረግ የከፈትናቸው የመሶብ ማዕከላት አስተዳደራዊ ሙስናን እየተከላከሉ የዜጎችን የአገልግሎት ርካታም እያሳደጉ ይገኛሉ።
ዜጎች ያለ ሥጋት የሙስናን ወንጀል ጥቆማ የሚሰጡበት ዲጂታል ሥርዓትም ተግባራዊ ተደርጓል።
ሙስናን ለመከላከል ዘላቂ መፍትሔው ትውልድን በሥነ ምግባር መገንባት፣ ተቋማትን ከብልሹ አሠራር መከላከል እና ለሙስና ወንጀል ተገቢውን የሕግ ማስከበር ሥራ መሥራት ይገባል።
በመሆኑም የፀረ ሙስና ትግሉ ስኬታማ እንዲሆን እና የመሶብ አገልግሎት እንዲጠናከር ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሠሩ ይገባል።

