(ኅዳር 26/2018 ዓ.ም) ሰላም ሚኒስቴር የአማራ ክልል መንግሥት እና የአፋሕድ ዘላቂ ሰላም ስምምነትን ተከትሎ የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፏል።
መንግሥት ለገጠሙን ችግሮች ውይይት እና ንግግርን ብቸኛ አማራጭ መንገድ መኾናቸውን እና ለዚህም ቁርጠኛ መኾኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል።
ቀድሞ የኃይል አማራጭን ተጠቅመው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች ይህንን የሰላም አማራጭ በመምረጥ ወደ ሰላማዊ መንገድ ሲመጡ መንግሥት ከግማሽ ርቀት በላይ በመሄድ በመቀበል ቁርጠኝነቱንም አሳይቷል።
ይህ መንገድ በሀገራችን የሰላም፣ የፍትሐዊ እና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ሥርዓትን ለመገንባት የሚያስችል ብቸኛው አማራጭ መኾኑንም መንግሥት ያምናል።
በዚህ አጠቃላይ መነሻ በአማራ ክልል ቀድሞ የኃይል አማራጭን ተጠቅመው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት የኃይል አማራጭ ለሕዝባችን ሰላም እና ለሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም እና ደህንነት ፋይዳ እንደሌለው በማመን ወደ ሰላማዊ መንገድ በመምጣት ድፍረት ያለው ውሳኔ አድርገዋል።
ይህ የሰላም አማራጭ ሁላችንንም አሸናፊ ስለሚያደርግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና ለአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት( አፋሕድ) ለወሰዱት ቆራጥ እርምጃ ያለውን አድናቆት በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ ይወዳል።
በሌላ በኩል አሁንም ቢኾን የትኛውም ጥያቄ ያለው አካል ለጥያቄው መልስ ለማግኘት ብቸኛ መፍትሔው ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርገውን መነጋገር እና መወያየትን መሠረት ያደረገ የሰላም መንገድ መኾኑን በማመን ኋላ ቀር የኾነውን የኃይል አማራጭ በመጠቀም የሚንቀሳቀሱ አካላት ተመሳሳይ የሰላም መንገድን እንዲመርጡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ጥሪ ያቀርባል።
የሰላም ሚኒስቴር
ሕዳር 26/2018 ዓ.ም

