ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከሞጣ ከተማ አሥተዳደር እና ከሁለት እጁ እነሴ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።
ውይይቱ “ዘካሪ፣ መካሪ የሀገር ሽማግሌ እና የሃይማኖት አባት ለዘላቂ ሰላም እና ልማት” በሚል መሪ መልዕክት ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
በውይይቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እዝ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ብርሃኑ ጥላሁን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ ሰላምን ለማረጋገጥ መወያየት እና የጋራ እሳቤ መያዝ ይገባል ብለዋል።
ሞጣ እና አካባቢው የመቻቻል፣ የመደጋገፍ እና የጠንካራ ማኀበራዊ ትስስር ባለቤት መኾኑን ተናግረዋል። ሞጣ እና አካባቢው ለሀገር ባለውለታዎችን ያፈራ እንደኾነም ገልጸዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን በከፍተኛ ችግር ውስጥ ቆይቷል፣ ማኅበራዊ እንቅስቃሴው ተጎትቶ ከርሟል ነው ያሉት።
አሁን ላይ በሰላም ወዳዱ ሕዝብ፣ በሀገር መከላከያ ሠራዊት እና በክልሉ የጸጥታ ኀይል ወደ አንጻራዊ ሰላም መመለሱንም ተናግረዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የጀመሩትን ትብብር አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለው እንዲገቡም ጥሪ አቅርበዋል። እስካሁን የሰላም አማራጭን የተቀበሉትን ምሥጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለሰላም ቀዳሚ እና ዘካሪ ናቸው ብለዋል።
የአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት የግጭት እንጂ የሰላም ትሩፋትን የመቋደስ ዕድል አልነበረውም ነው ያሉት።
ባለፉት ዓመታት የእሴት መሸርሸር ገጥሟል፤ ንጹሐን በግፍ ተገድለዋል፤ የሞቱት እንዳይቀበሩ ኾነዋል፤ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተዋርደዋል ብለዋል። ክልሉን ዋጋ የሚያስከፍል የሰብዓዊ ልማት ስብራት ገጥሞ መቆየቱንም ተናግረዋል።
ተማሪዎች የማይማሩበት፣ አርሶ አደሮች የማያርሱበት፣ ነጋዴዎች የማይነግዱበት፣ ማኀበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የተገታበት እንደነበር አስታውሰዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ባሉበት ሀገር ሕዝብ እና ሀገር የሚጎዳ ችግር ገጥሞ መቆየቱንም ገልጸዋል።
ወንድማማችነትን የሚሸረሽር ችግር ገጥሞ እንደቆየም አንስተዋል። በውይይት ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ሰላም ሐቀኛ ውይይትን እና ዕውነት መናገርን ይፈልጋል ነው ያሉት። በመወያየት ልማትን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል።

