በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት መካከል ዘላቂ የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ስምምነቱ ሁሉንም አሸናፊ ያደረገ፤ ለአማራ ክልል ሕዝብ የዘላቂ ሰላም ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠ መሆኑን ተፈራራሚዎቹ ገለጹ።
ስምምነቱን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅትን በመወከል ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ ትላንት ፈርመዋል።
ከታሪካዊ ጠላቶች እና ከሌሎችም ጋር በጥቅም ተሳስሮ በክልሉ እና በሀገር ላይ የውክልና ጦርነት ማድረግ ታጋይነት ሳይሆን ባንዳነት ነው ሲሉ የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅትን (አፋሕድ) በመወከል የተፈራረሙት ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በበኩላቸው ስምምነቱን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ የሰላም ስምምነቱ የተፈረመበት ዕለት ለአማራ ሕዝብ ታሪካዊ ቀን ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ተኩል ዓመታት የክልሉ ሕዝብ በግጭት አዙሪት ውስጥ መቆየቱን ተናግረው፣ ይህም ህይወት የቀጠፈ፣ በርካታ ህጻናትን ከትምህርት ገበታ ውጭ ያደረገ እና የተለያዩ የመሠረተ ልማት ውድመት ያስከተለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ህዝብ ከስምምነቱ ተጠቃሚ መሆኑን አንስተው፤ በስምምነቱ ከምንም በላይ የአማራ ችግሮችን በውይይት የመፍታት እሴቶች የታዩበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዘላቂ ሰላም በክልሉ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ለማጠናከር መሰረት መሆኑን በመግለጽ፤ ስምምነቱም በክልሉ የሰላም ሁኔታ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያን በራሷ ልጆች የማተራመስ ዓላማ ያላቸውን የውጭ ኃይሎችን ፍላጎት ባለመቀበል ወደ ሰላም መጥተናል ያሉት ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ በበኩላቸው፣ የሰላም ስምምነቱ ታሪካዊ መሆኑን ገልጸዋል።
ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት እና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በጋራ ለማስከበር የሰላም ስምምነቱን መፈራረማቸውን ተናግረዋል፡፡
ካፒቴን ማስረሻ አክለውም፣ የባዕዳንን አጀንዳ ተሸክመው የሚንቀሳቀሱ ሌሎች ኃይሎችም የእነርሱን ትክክለኛ ፈለግ በመከተል ወደ ሰላም እና ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲመጡ ጠይቀዋል፡፡
የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት የመረጃ ደህንነት መመሪያ ኃላፊ እና የኮር ስራ አስፈጻሚ መስፍን አባተ በበኩላቸው፤ የሰላም ስምምነቱ የጠላቶች አጀንዳ የተሰበረበት በመሆኑ ታሪካዊ ነው ብለዋል፡፡
ወደ ስምምነቱ ያልገቡ ሌሎች አደረጃጀቶች አሁን ያነገቡት አጀንዳ የአማራ ህዝብን የማይጠቅም መሆኑን ተረድተው ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲመጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

