የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የክልሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጉባኤ በጥምረት ያዘጋጁት አራተኛው ዓለም አቀፍ የጤና ጉባኤ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
ጉባኤው “ምርምርን ወደተግባር መቀየር፣ በችግር ውስጥ ኾኖም የኅብረተሰብ ጤና ሥርዓትን ማጠናከር” በሚል ጭብጥ ነው የሚካሄደው።
የጤና ችግሮችን ሳይንሳዊ በኾኑ መንገዶች መፍታት የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች በጉባኤው ላይ ቀርበው ውይይቶች ይደረጋሉ።
ውሳኔ ሰጭ አካላትም እነዚህ ምርምሮች ወደተግባር ገብተው ለውጥ እንዲያመጡ የድርሻቸውን የሚወስዱበት ጉባኤ ነው።
በጉባኤው ላይ የፌዴራል እና የክልል መሪዎች ይሳተፉበታል። ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ ምሁራንም የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ያቀርባሉ።
በመድረኩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ክልሉ የተለያዩ ወረርሽኞች ለመቆጣጠር በሚተጋበት ወቅት ይህ ጉባኤ መካሄዱ ለሥራዎች ስኬት ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት ካሳለፍነው የጸጥታ ችግር ጋር ተደማምረው የተለያዩ ወረርሽኞች ሕዝባችንን እና ተቋሙን ቢፈትኑም በኅብረት በሚከናወኑ ጠንካራ ሥራዎች መቆጣጠር እና ችግሮችን ሁሉ ማለፍ ተችሏል ብለዋል።
ይህም በጋራ መሥራት ለውጤት እንደሚያበቃ የተረጋገጠበት እንደኾነ አመላክተዋል።
አሁንም ቢኾን የማይናጋ እና ዘላቂ የጤና ሥርዓት መገንባት ያስፈልጋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ የዛሬው ዓለም አቀፍ ጉባኤም ለዚህ አጋዥ ነው ብለዋል ሲል የዘገባው አሚኮ ነው።

