(ኅዳር 25/2018 ዓ.ም) በአማራ ክልል በቀጣይ አምስት ዓመት 5 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች ተደራሽ ይሆናል የተባለው ዲጅታል አማራ ኢንሼቲቭ ውይይቶችና ስልጠናዎች በትምህርት ተቋማት ተጀምሯል፡፡
በተመረጡ ዞኖችና የትምህርት ተቋማት ትናንት በተጀመረው የፕሮግራም ትውውቅ መድረክና የአሰልጣኞች ስልጠና ማስጀመሪያ መርሃግብር ላይ የተገኙት የአማራ ፕሬዜዴንሻል ዴሊቨሪ ዩኒት አስተባባሪ አቶ ሞገስ ተካ ፕሮግራሙ አዲስ መሆኑና የክልሉ ፕሬዜዳንት ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በሩዋንዳ በተደረገ ጉብኝት የተገኘ ተሞክሮ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት አራት ወራትም ከዘርፉ ምሁራን ጋር ፕሮግራሙን ለማስጀመር የሚያስችሉ የተለያዩ የማስተማሪያ ሞጁሎችና ቪዲዮች ሲዘጋጁ መቆየታቸውን የገለጹት ሃላፊው በቀጣይ ወደ ዲጅታላይዜሽን በሚደረገው ጉዞ ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት በሚደረገው ርብረብ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ሀላፊ ወ/ሮ እየሩስ መንግስቱ በበኩላቸው አለም በተለያዩ ጊዚ የተለያዩ የመወዳደሪያ መስፈርቶችን ያስቀምጣል አሁን ያለው የአለም መወዳደሪያ ቲክኖሎጅ ነው ያሉት ሃላፊዋ በዚህ ዘመን የብዙ ሰዎችን ጉልበት የሚተካና 24 ሰዓት የሚሰራ ሮቦት በተፈጠረበት ዘመን ከቴክኖሎጅ መራቅ የማይቻል ነው ብለዋል፡፡
የትምህርት ስርዓቱ ቴክኖሎጅ መር እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ወ/ሮ እየሩስ ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ የአይሲቲ ትምህርት መጀመሩና በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተጀመረው ከቴክኖሎጅ ጋር የተገናኙ የሙያ ትምህርቶች መጀመራቸው የዚህ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የውይይት መድረኩን የመሩት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ም/ሃላፊ አቶ ደምስ እንድሪስ የትምህርት ተቋሙ በቀጣይ ወደ ዲጅታል ኢኮኖሚ የሚደረገውን ጉዞ ተረድቶ አለማቀፍ ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት ተቋሙ ግንባር ቀደም ሆኖ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በቴክኖሎጅ የተሟሉ የመማሪያ ክፍሎችን ማዘጋጀትና ዜጎች በዲጅታል አለም ውስጥ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ በሚደረገው ጥረት የሚገጥሙ ችግሮችን ተቋቁሞ ፕሮግራሙን ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያለውን የኢንተርኔት ተደራሽነትና የኮምፒውተር ግብዓት ተጠቅመን ፕሮግራሙን ውጤታማ ለማድረግ እንሰራለን ብለዋል፡፡
በቀጣይም የቴክኖሎጅ ግብአቶችን ማሟላትና ወደ ዲጅታላይዜሽን የሚደረገውን ጉዞ ማሳለጥ ከሁሉም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሰፊ ስራ እንደሚጠበቅ በውይይቱ ተገልጿል፡፡

