(ኅዳር 05/2018 ዓ.ም) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ “በጎነት ለጤናችን” በሚል መልዕክት ሲያከናውን የቆየውን የ2017 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማጠቃለያ እና የእውቅና መርሐ ግብር አካሂዷል፡፡
በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በጤናው ዘርፍ ሰው ተኮር የኾኑ የነጻ ሕክምና፣ የደም ልገሳ መርሐ ግብር፣ የአቅመ ደካማ ዜጎችን ቤት ማደስ፣ ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ማሰባሰብ፣ ተላላፊ እና ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎችን ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ መመርመር እና እንዲታከሙ ማድረግ፣ በጤና ተቋማት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ማካሄድ እና ሌሎች ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸው በመርሐ ግብሩ ተጠቅሷል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ ሰይድ የሱፍ በከተማዋ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራው የሕክምና አገልግሎት፣ የቲቢ በሽታ ልየታ፣ የክትባት አገልግሎት፣ የማሕጸን በር ካንሰር ምርመራ፣ የደም ልገሳ እና ሌሎች አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በመደበኛው የሕክምና ሥርዓት ተደራሽ ያልኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
የሰሜን ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ደሳለኝ ዳምጤ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራው በተሰበሰው የደም ልገሳ አማካኝነት በዞኑ ሆስፒታሎችን እና ጤና ጣቢያዎችን የደም እጥረት እንዳይኖር አድርጓል ነው ያሉት፡፡
ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት የተሠራበት መኾኑ ልምድ ሊወሰድበት የሚችል እንደኾነም ጠቅሰዋል፡፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራው በማኅበረሰቡ ውስጥ የግንዛቤ ማሳደግ ሥራዎች የተሠሩበት እንደኾነ ተናግረዋል።
በጤናው ዘርፍ የተሠራው የበጎ ፈቃድ ሥራ የሰብዓዊነት ተግባር የተገለጠበት እንደኾነም ገልጸዋል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከ6 ሚሊዮን በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረገ እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡
በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከ82 ሺህ በላይ ዩኒት ደም በመሰብሰቡ በምንም የማይተካ የሕይወት አድን ሥራ መካሄዱን ተናግረዋል፡፡
ተቋማትን ለሕክምና አገልግሎት ምቹ በማድረግ የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል፡፡ እነዚህ ሥራዎች በክረምት ብቻ ሳይኾን ማኅበራዊ መሥተጋብራችንን አጠናክረን በበጋ ወራትም መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ መስፍን አበጀ (ዶ.ር) በክልሉ ሁሉንም አቅሞች በማስተባበር እና በማቀናጀት የበጎ ፈቃድ ማኅበራዊ አገልግሎት ተግባራዊ ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡
ይህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባሕል ኾኖ እንዲቀጥል ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል። በቀጣይም ክፍተቶችን እየለዩ በትኩረት መሥራት እና በፈጠራ ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል ሲል የዘገበው አሚኮ ነው፡፡

