በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚሠራጩ መድኃኒቶች ባሕር ዳር ከተማ ገቡ።

(ኅዳር 05/2018 ዓ.ም) በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ጤና ተቋማት የሚሰራጩ ልዩ ልዩ መድኃኒቶችን የጫኑ 17 ከባድ ተሽከርካሪዎች ባሕር ዳር ከተማ ገብተዋል።

መድኃኒቶቹ በኢትዮጵያ መንግሥት ወጭ የቀረቡ ሲኾን የኢትዮጵያ ጤና ልማት እና ጸረ ወባ ማኅበር ደግሞ የማጓጓዝ እና የሥርጭት ሥራውን በዋናነት እያስተባበረ ነው። የአሜሪካ መንግሥት ደግሞ የመድኃኒቶቹን የማጓጓዣ ወጭ ድጋፍ አድርጓል።

መድኃኒት የጫኑ ተሽከርካሪዎችን እያስተባበሩ ባሕር ዳር ከተማ የተገኙት የኢትዮጵያ ጤና ልማት እና ጸረ ወባ ማኅበር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አክሊሉ ጌትነት መድኃኒቶቹ ወደ ክልሉ መግባታቸው በተለይም ወቅታዊ የወባ በሽታ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ አይነተኛ ሚና ይኖራቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጤና ልማት እና ጸረ ወባ ማኅበር “ለወገን ደራሽ ወገን ነው” በሚል መልዕክት በተለይም የወባ ወረርሽኝን ለመግታት ከ27 ዓመታት በፊት የተቋቋመ ማኅበር ነው ብለዋል።

ዛሬም በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የቀረቡ መድኃኒቶች ከዋናው መጋዝን ጀምረው ያለምንም የጸጥታ ችግር ወደ አማራ ክልል ባሕር ዳር ከተማ ይዘው መግባታቸውን አንስተዋል።

ባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው ማዕከል ላይ የሚራገፉ መድኃኒቶች እንደሚኖሩ እና ቀሪው ደግሞ ወደ ጎንደር ከተማ ማዕከል እንደሚጓጓዝም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ቀሪው የማጓጓዝ ሥራም ያለምንም የጸጥታ ችግር እና በስኬት ተጓጉዞ በታቀደለት ቦታ ይደርሳል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ጤና ልማት እና ጸረ ወባ ማኅበር መድኃኒቶችን ከመጋዝን ጀምሮ እስከተጠቃሚዎች ድረስ በስኬት እንዲደርሱ የማጓጓዝ ሥራውን በማስተባበር ሀገራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝም አቶ አክሊሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ሥራ አሥኪያጅ እና የሰሜን ምዕራብ ክላስተር አሥተባባሪ አምሳሉ ጫኔ እንዳሉት የመድኃኒቶች መምጣት የክልሉ ጤና ተቋማት የሚገጥሟቸውን የመድኃኒት እጥረት በመፍታት የጤና ሥርዓቱን የሚያሻሽል ነው ብለዋል።

የመጡ መድኃኒቶች በነጻ የሚታደሉ ክትባቶችን እና ቋሚ በሽታዎችን የሚያክሙ ስለመኾናቸውም ገልጸዋል።

መድኃኒቶችን በስኬት የማጓጓዝ ሥራውን ያከናወነውን የኢትዮጵያ ጤና ልማት እና ጸረ ወባ ማኅበር እና የሎጅስቲክስ ድጋፍ ያደረገውን የአሜሪካ መንግሥትም አመሥግነዋል።

ወደ ማዕከላት የገቡ መድኃኒቶች ወደጤና ተቋማት ተጉዘው ለተጠቃሚዎች እስከሚሰራጩ ድረስ የድጋፍ እና ክትትል ሥራዎች እንደሚከናወኑም አቶ አምሳሉ ተናግረዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top