(ኅዳር 04/2018 ዓ.ም) በአማራ ክልል እየተከናወኑ ያሉ የፌደራል የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በውይይቱም በግንባታ ላይ ያሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም እና የትኩረት አቅጣጫዎች የሚያመላክት ዝርዝር ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡
በክልሉ በግንባታ ላይ ባሉ ፕሮጀክቶች የውጤታማነት፣ የወሰን ማስከበር፣ የካሳ ግምት መጋነን እና በወቅቱ መረጃ አለመላክ ችግሮች እንዳሉ ተገልጿል።
ፕሮጀክቶችን በባለቤትነት ይዞ የመገምገም፣ የመከታተል፣ የመደገፍ እና የመምራት ክፍተቶች፤ በአንዳንድ ፕሮጀክቶች ጸጥታን ሽፋን በማድረግ ተቋራጮች የሚፈጥሩትን መስተጓጎል ፈጥኖ ያለመፍታት ውስንነቶች እንደሚታዩም ተመላክቷል።
የሥራ ተቋራጮች አቅም ማነስ፣ የተቋራጮች ክፍያ መዘግየት፣ የግብዓት አቅርቦት፣ የካሳ ክፍያ ችግር፣ ምክንያት እየፈጠሩ ሥራ በሚያጓትቱ አንዳንድ ፕሮጀክቶች ላይ ተጠያቂነት አለማስፈን እና ግንባታቸው ከተጀመረ በኋላ የሚነሱ የዲዛይን ማሻሻያ ሥራዎች ሌሎች ችግሮች ናቸው ተብሏል።
የመንገድ ጥገና ተደራሽነት እና ጥራት ጋር የተያያዙ ክፍተቶች አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸው ተገምግሞ የፕሮጀክቶችን የላቀ የመፈጸም አቅም እና ውጤታማነት ማረጋገጥ የሚያስችል የቀጣይ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
ለፕሮጀክቶቹ መዘግየት መንስኤ የኾኑ ችግሮችን በመቅረፍ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እና ዕቅድ ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው የቅርብ ክትትል እና ድጋፍ የሚያደርግ ግብረ ኀይልም ተቋቁሟል ሲል የዘገበው አሚኮ ነው፡፡

