ኢትዮጵያ ልዩ ጥንካሬ እና የእድገት ፍጥነት አሳይታለች

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የመቶ ቀን እቅድ ግምገማ የአለምን የኢኮኖሚ አዝማሚያ፣ የኢትዮጵያን ማክሮኢኮኖሚ የመጀመሪያ ሩብ አመት አፈፃፀም እንዲሁም የእድገት አዝማሚያን እና አጠቃላይ ምልከታን ያካተተ አቅርቦትን አካትቷል።

በአለም የኢኮኖሚ ልማት አውድ ስንመለከት ኢትዮጵያ ልዩ ጥንካሬ እና የእድገት ፍጥነት አሳይታለች።

በ2017 የበጀት አመት የኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢኮኖሚ አፈፃፀም በጥንካሬው በመቀጠል 9.2 በመቶ አመታዊ የGDP እድገት አሳይቷል።

ይኽም 7.3 በመቶ በሆነ ጠንካራ የግብርና ውጤት መስፋፋት፣ በ13 በመቶ የኢንደስትሪ እድገት ብሎም በ7.5 በመቶ የአገልግሎት ዘርፍ እድገት የተገለፀ ነበር።

የሀገራችን የGDP ተዋፅኦም በብዝኃ መሠረት እየያዘ መሄዱን የሚያሳይ ሲሆን ይኽም በግብርና 31.3 በመቶ፣ በኢንደስትሪ 30.2 በመቶ እና በአገልግሎት 39.6 በመቶ አስተዋፅኦ የታየ ነው።

እየተካሄዱ በሚገኙ የለውጥ ሥራዎች፣ በመንግሥት እየተከወኑ ባሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እና አዲስ ኢንቨስትመንቶች በመደገፍ በ2018 ዓመተ ምኅረት ኢኮኖሚያችን በ10.2 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል።

እንደ የታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ብሎም እንደ የማዳበሪያ ማምረቻ እና የተፈጥሮ ጋዝ ልማት ሥራ ጅማሮዎች የኢኮኖሚ እድገቱን የበለጠ እንደሚያነቃቁ ይጠበቃል። የየዘርፉ የእድገት ትንበያም ጠንካራ ውጤት እንደሚገኝ ያመለክታል።

ግብርና በ7.8 በመቶ፣ በአዳዲስ የማኑፋክቸሪንግ ፕሮጀክቶች እና የተሻሻሉ ግብዓቶች የተጠናከረው ኢንደስትሪ 13.2 በመቶ እንደሚያድጉ የተተነበየ ሲሆን ማዕድን ለ2018 የተቀመጠለትን ግብ እንደሚበልጥ ይጠበቃል።

በተጨማሪም የአገልግሎት ዘርፉ እድገት በሚያሳዩት የንግድ እንቅስቃሴ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የቱሪዝም ፍሰት እና የዲጂታል ኢኮኖሚ መስፋፋት በመጠቀም 9.3 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል።

የውጭ ንግድ 2.5 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን ይኽም እቅዱን እና የባለፈውን አመት ተመሳሳይ ጊዜ አፈፃፀም የበለጠ ሆኖ ታይቷል።

የፋይናንስ ዘርፉ የልማት ሥራዎችን እና ኢንቨስትመንትን በመደገፍ እና ቁልፍ ሚናውን እየተወጣ ሲሆን በመጀመሪያው ሩብ አመት 113 በመቶ የሆነ ከቀደመው ተመሳሳይ ጊዜ ብልጫ ያለው የብድር አቅርቦት አቅርቧል።

የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትም እየተጠናከረ መሄዱን የቀጠለ ሲሆን በሶስት ወራት ብቻ 6.5 ትሪሊዮን ብር የተንቀሳቀሰበት ደረጃ ደርሷል።

አጠቃላይ አፈፃፀሙ በሁሉም መስኮች የተሻለ ውጤትን የሚያሳይ ሲሆን ይኽም ኢትዮጵያ ወደ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ብሎም ዘላቂ እና አካታች የኢኮኖሚ እድገት የምታደርገውን ፈጣን ሂደት የሚያረጋግጥ ነው።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top