የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ ከክልል እስከ ዋና ክፍል ኃላፊዎች እንዲሁም የሁሉም ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዦች ተገኝተዋል።
በውይይቱ የተገኙ በአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የፖለቲካና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) እንደተናገሩት ለክልላችን ብሎም ለሀገራችን ለዘመናት የዘለቀ የግጭት አዙሪት ውስጥ መዘፈቅ ዋነኛ ምክንያት ውስጣዊ ባንዳዎች ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በሚሰሩት አሻጥር ነው ብለዋል።
የሀገራችን ሰላም እና ልማት ደስታ የማይሰጣቸው የውጭ ጠላቶቻችን በእጅ አዙር ለሚፈፅሟቸው ሴራዎች ፈፃሚ መሆን የዘመናት አኩሪ ታሪካችንን የሚሸረሽር እና የታሪክ ተወቃሽ የሚያደርግ ተግባር ነው ሲሉም ዶክተር ዘሪሁን ፍቅሩ አክለው ተናግረዋል።
ጸረ-ሰላም ኃይሎች ከታሪካዊ ጠላቶቻችን አጀንዳ በመቀበልና ህዝባችንን በሰላም እጦት እያስቸገሩ ነው ያሉት ዶክተር ዘሪሁን እነዚህ አካላት የሚፈፅሙትን ዕኩይ ተግባር ማክሸፍ ይኖርብናል ብለዋል።
በአማራ ህዝብ ጥያቄ ሽፋን የሚፈፀም ማንኛውም ህገ-ወጥ ተግባር ተቀባይነት የሌለውና የማህበረሰባችንን ባህልና ወግ የማይመጥን መሆኑም ዶክተር ፍቅሩ አስታውቀዋል።
ኮማንደር ንጉሴ ሞገስ የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ህገ-ወጥ ቡድኖች የክልላችንን ሰላም በማወክ ተጠምደው ማህበረሰባችንን ለመከራ መዳረጋቸውን አንስተው በዞናችን ሰላምን ለማስጠበቅና ህግ ለማስከበር በተሰሩ ጠንካራ ስራዎች በበርካታ አካባቢዎች ሰላም ማስፈን ተችሏል ብለዋል።
የዞኑ የፀጥታ ኃይል፣ ከፌደራል የፀጥታ ኃይልና ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን ባደረገው የህዝብ ግንኙነት ስራ በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ተደርጓል፣ በዚህም ማህበረሰባችን አብዝቶ ሲፈልገው የነበረውን ሰላም በአንፃራዊነት መመለስ ተችሏል ሲሉ ኮማንደር ንጉሴ ገልጸዋል።
በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ወለላው ተገኘ በበኩላቸው ዞኑ በታሪካዊ ጠላቶቻችን ተላላኪ ባንዳዎች ሊከሰቱ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን በራስ አቅም ለመከላከል የጸጥታ መዋቅሩ ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን በቆራጥነት እየሰራን እንገኛለን።
የዞናችን ህዝብ ሰላሙ እና ደኅንነቱ ተረጋግጦ የልማት ተጠቃሚ ተጠቃሚ እንዲሆን ቀን ከሌት እየሰራን እንገኛለን በማለት ኮማንደር ወለላው አብራርተዋል።
